Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የሎጎ ሐይቅ ሪዞርትን መረቁ

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)በዛሬው ዕለት የሎጎ ሐይቅ ሪዞርትን በይፋ መርቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ ሪዞርቱ የወሎን ተፈጥሯዊ ውበት፤ ዘመናዊ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ደረጃውን ከጠበቀ መሠረተ ልማት ጋር አጣምሮ የያዘ ድንቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ሪዞርቱ ከሚታየው ገጽታው ባለፈ ለአካባቢው እና ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት መፋጠን ትልቅ አንቀሳቃሽ ፕሮጀክት መሆኑን አውስተዋል፡፡
ከጎርጎራ በመቀጠል በአማራ ክልል የ’ገበታ’ ውጥን ሁለተኛው ፕሮጀክት እንደመሆኑ መጠን፤ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር በግብርና፣ በትራንስፖርት፣ በቱሪዝምና በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ከፍተኛ መነቃቃትን ይፈጥራል ነው ያሉት።
ይህም ለአካባቢው አምራቾች፣ ለዕደ ጥበብ ባለሙያዎችና ለሥራ ፈጣሪዎች አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን በማመቻቸት ለቱሪዝም መር ዕድገትና ለዘላቂ የኑሮ ዋስትና ትልቅ መሠረት እንደሚጥል አመልክተዋል፡፡
‎በመደመር መንፈስ የተመራው ይህ ፕሮጀክት፤ መንግሥትንና የግሉን ዘርፍ በአንድ ገበታ በመሰየም ፖሊሲን ወደ ተግባር፣ ኢንቨስትመንትን ደግሞ ወደ ተጨባጭ ውጤት ለውጧል ብለዋል።
ይህ በትብብር የተገነባው ሪዞርት ለመንግሥትና ለግሉ ዘርፍ አጋርነት (PPP)፣ ለፖሊሲ ቀጣይነትና ለረጅም ጊዜ ዕድገት ዘላቂ መሠረት በመጣሉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
‎ከምንም በላይ ደግሞ ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት፤ ገራገር እና ቅን የሆነው የወሎ ሕዝብ ውብ ቅርሶቹን ፣ ባህሉን፣ እሴቶቹንና ድንቅ እንግዳ ተቀባይነቱን ለዓለም እንዲያጋራ የቀረበ ትልቅ ግብዣ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።
Exit mobile version