አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በአማራ ክልል የ’ገበታ’ ውጥን ሁለተኛ ፕሮጀክት የሆነውና በሐይቅ ከተማ የሚገኘው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርትን በይፋ መርቀዋል፡፡
ሪዞርቱ የወሎን ተፈጥሯዊ ውበት፤ ዘመናዊ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሠረተ ልማቶችን አጣምሮ የያዘ ድንቅ ፕሮጀክት ነው።
አጠቃላይ ፕሮጀክቱ 13 ነጥብ 3 ሔክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን÷ ባለመዓዛ ተክሎችና ውብ የአረንጓዴ ስፍራዎችን በውስጡ አካትቷል።
የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት በውስጡ 3 ነጥብ 70 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የአስፋልት መንገድ፣ በ67 ክፍሎች 80 አልጋዎች፣ ሙሉ ስፓ፣ የመዋኛ ገንዳዎች፣ የውስጥና የውጭ የስፖርት ማዘውተሪያ ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ስፍራዎችን ይዟል።
በተጨማሪም በአንዴ ከ100 በላይ መኪናዎችን መያዝ የሚያስችል የመኪና ማቆሚያ እና የሔሊኮፕተር ማረፊያ ስፍራን ያካተተ ነው።
ሪዞርቱ ከሚታየው ገጽታው ባለፈ ለአካባቢው ብሎም ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት መፋጠን ትልቅ አንቀሳቃሽ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።
ፕሮጀክቱ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር በግብርና፣ በትራንስፖርት፣ በቱሪዝምና በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ከፍተኛ መነቃቃትን እንደሚፈጥር አስገንዝበዋል።
ይህም ለአካባቢው አምራቾች፣ ለዕደ ጥበብ ባለሙያዎችና ለሥራ ፈጣሪዎች አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን በማመቻቸት ለቱሪዝም መር ዕድገትና ለዘላቂ የኑሮ ዋስትና ትልቅ መሠረት ይጥላል ነው ያሉት።

