አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ለቱሪዝም መር ዕድገት እና ለዘላቂ የኑሮ ዋስትና ትልቅ መሠረት ይጥላል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በአማራ ክልል ከጎርጎራ በመቀጠል የ’ገበታ’ ውጥን ሁለተኛ ፕሮጀክት የሆነውን የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት መርቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ ሪዞርቱ የወሎን ተፈጥሯዊ ውበት፤ ዘመናዊ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ደረጃውን ከጠበቀ መሠረተ ልማት ጋር አጣምሮ የያዘ ድንቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ሪዞርቱ ለአካባቢውም ሆነ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት መፋጠን ትልቅ አንቀሳቃሽ ፕሮጀክት መሆኑን ነው ያወሱት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቱ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር በግብርና፣ በትራንስፖርት፣ በቱሪዝምና በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ከፍተኛ መነቃቃትን እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
ይህም ለአካባቢው አምራቾች፣ ለዕደ ጥበብ ባለሙያዎችና ለሥራ ፈጣሪዎች አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን በማመቻቸት ለቱሪዝም መር ዕድገትና ለዘላቂ የኑሮ ዋስትና ትልቅ መሠረት ይጥላል ነው ያሉት።
ፕሮጀክቱ በመደመር መንፈስ መመራቱንና መንግሥት የግሉን ዘርፍ በአንድ ገበታ በመሰየም ፖሊሲን ወደ ተግባር፣ ኢንቨስትመንትን ደግሞ ወደ ተጨባጭ ውጤት መለወጡን አንስተዋል።
በትብብር የተገነባው ሪዞርት ለመንግሥትና ለግሉ ዘርፍ አጋርነት (PPP) እንዲሁም ለፖሊሲ ቀጣይነትና ለረጅም ጊዜ ዕድገት ዘላቂ መሠረት የጣለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት፤ ገራገር እና ቅን የሆነው የወሎ ሕዝብ ውብ ቅርሶቹን፣ ባህሉን፣ እሴቶቹንና ድንቅ እንግዳ ተቀባይነቱን ለዓለም እንዲያጋራ የቀረበ ትልቅ ግብዣ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።

