አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተናን መቶ በመቶ በበይነ መረብ ለመስጠት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው አለ የትምህርት ሚኒስቴር፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እንዳሉት÷ በተያዘው በጀት ዓመት የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ ይሰጣል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ፈተናው በወረቀትና በበይነ መረብ ሲሰጥ እንደረበር አንስተው÷ በዚህ ዓመት ፈተናውን በበይነ መረብ ብቻ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም የተለያዩ ግብዓቶች ለክልሎች ድጋፍ እየተደረገ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ÷ በፈተና ጣቢያዎች በቂ የኢንተርኔት አቅርቦት እንዲኖር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።
ክልሎች በዚህ ሒደት የሚያጋጥሙ ችግሮች እንዳይኖሩ በቂ ኮምፒዩተር፣ ኔትዎርክና አማራጭ የሀይል አቅርቦት እንዲኖር ልዩ ትኩረት ሰጥተው መዘጋጀት አለባቸው ነው ያሉት፡፡
ለተማሪዎች በቂ ሥልጠና መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።
ትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት ምዘናና ፈተና አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ያጋጠሙ ስብራቶችን ለማስቀረት የተለያዩ የሪፎርም ተግባራትን ቀርጾ ፈተናን ከስርቆትና ኩረጃ በፀዳ መልኩ ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል።
ባለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተናን በበይነ መረብ የወሰዱ ተማሪዎች ቁጥር 134 ሺህ 828 ሲሆን፤ ይህም ከአጠቃላይ ተፈታኞች አንጻር 23 ነጥብ 2 በመቶ ነበር።

