አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ መንግሥታት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚያጠናክሩ የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ እና የፈረንሳይ በአውሮፓ ህብረትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ልዑክ ኤሌኖር ካሮይት ተፈራርመዋል፡፡
በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ የተፈረመው ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ አጋርነት ለማጠናከር እና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥራን ለመደገፍ ያለመ ነው፡፡
አቶ አሕመድ ሺዴ ፈረንሳይ እንደ የአበዳሪ ኮሚቴ ተባባሪ ሊቀመንበርነቷ እያደረገች ያለውን ወሳኝ ሚና አድንቀው÷ ኢትዮጵያ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለመፍጠር ትብብርን ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
በፈረንሳይ እና በአውሮፓ ማሕበረሰብ የሚደገፉ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቮችን ጨምሮ በቀጣናው ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ማጣጣም እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
ኤሌኖሬ ካሮይት በበኩላቸው ለረጅም ጊዜ የቆየውን የአውሮፓ ህብረት እና የኢትዮጵያ አጋርነት አስፈላጊነት ገልጸው÷ ስምምነቶቹ በጋራ መከባበር፣ በጋራ እሴቶች እና ለዘላቂ እድገት የጋራ ቁርጠኝነት ላይ የተመሠረቱ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ትብብሩ ከኢትዮጵያ የሪፎርም አጀንዳ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ጠቅሰው÷ የፈረንሳይ የልማት ተቋማት በኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት ፋይናንስ ውስጥ ስትራቴጂካዊ ሚና መጫወታቸውን ቀጥለዋል ብለዋል።
የጋራ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ለማምጣት እና የኢትዮጵያን ተወዳዳሪነት ለማስቀጠል ተለዋዋጭ እና ለባለሃብቶች ተስማሚ የንግድ ሁኔታ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
በስምምነቱ መሰረት ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ሁለተኛ ምዕራፍ ማስፈጸሚያ የሚውል የ80 ሚሊየን ዩሮ በጀት እና እና 1 ነጥ 5 ሚሊየን ዩሮ የቴክኒክ ድጋፍ አድርጋለች፡፡
እንዲሁም በቡድን 20 አባል ሀገራት የጋራ ማዕቀፍ ስር ከሁለትዮሽ አበዳሪዎች ጋር የተደረገ የመጀመሪያው ታሪካዊ የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት መፈራረማቸውን ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
በተጨማሪም ሀገራቱ በኢንቨስትመንት እና ሌሎች ዘርፎች ያላቸውን ሁለንተናዊ ትብብር ማጠናከር የሚያስችል ስምምነት መፈራራማቸው ነው የተገለጸው፡፡
ለአብነትም ፈረንሳይ በቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ላይ ለመሳተፍ እንድምትፈልግ ተጠቁሟል፡፡
በዮናስ ጌትነት

