Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ስኬት ለማስቀጠል ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እሰራለሁ – የዓለም ባንክ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ ይቀጥላል አሉ የባንኩ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቤርዴ፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከማኔጂንግ ዳይሬክተሯ እና ከባንኩ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ምክትል ፕሬዚዳንት ንዲያሜ ዲዮፕ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን ጨምሮ ለዘላቂና አካታች ልማት እንዲሁም የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚን ለማረጋገጥ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡

አቶ አህመድ ሺዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ በግሉ ዘርፍ የሚመራ ኢኮኖሚን ለመገንባት የምታደርገውን ሽግግር ለማፋጠን የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡

በዚህም የግሉን ዘርፍ የልማት እድሎች ለማስፋትና የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ትግበራ ለማጠናከር የዓለም ባንክ ቀጣይነት ያለው ትብብር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ አና ቤርዴ በበኩላቸው፥ በገንዘብ ፖሊሲ አስተዳደር፣ የዋጋ ንረት ጫናን በመቀነስ፣ የውጭ ምንዛሪ ክምችትን በማሳደግ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ገበያን በማጠናከር ረገድ የተከናወኑ ተግባራትን አድንቀዋል፡፡

ባንኩ በኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍና የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን አቅም በማሳደግ ለኢኮኖሚ ማሻሻያውና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የረዥም ጊዜ የልማት ዘርፎች ውጤታማነት ለማረጋገጥ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ሁለቱ ወገኖች በስራ እድል ፈጠራ፣ በኢነርጂ ልማት፣ በሎጅስቲክስ፣ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ በግብርና፣ በግሉ ዘርፍ፣ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቋቋም ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡

በተጨማሪም በማሻሻያው የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠል የተቋማትን አቅም ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት፥ አካታች ልማትና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

Exit mobile version