Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት፣ ሥልጣኔና ብልጽግና ንጋት አብሣሪ ሆና ቀጥላለች – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት፣ ሥልጣኔ እና ብልጽግና ንጋት አብሣሪ ሆና ቀጥላለች አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ኢትዮጵያ የቀደምት ሥልጣኔዎች እናት፤ ባርነትን ታግለው ያሸነፉ የክንደ ብርቱዎች ምድር ናት ብለዋል።

ሺህ ዘመናትን ቀድማ የሥልጣኔን ቀለም ያሠመረች፣ ጀግንነትን በተራሮቿ ደረት ያተመች፤ ዛሬም አኅጉራዊ ብልጽግናን አውጃ እየሠራች ያለች የአሕጉሩ ዐቅም እና ጌጥ ናት ነው ያሉት።

39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በመጪዎቹ ሁለት ቀናት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አስታውሰው÷ በጉባዔው የሚሳተፉ የሀገራት መሪዎችና የልዑካን ቡድኖቻቸው ወደ መዲናቸው እና ወደ ሁለተኛ ቤታቸው በመግባት ላይ ናቸው ብለዋል።

እኛ ኢትዮጵያውያንም በደመቀ እንግዳ ተቀባይነት አርሂቡ ብለን እየተቀበልናቸው ነው በማለት ገልጸው÷ በመሪዎች ጉባዔ ላይ የአኅጉሪቱ በትናንት ጥረት እና ስኬት እንዲሁም በነገ ብሩህ ተስፋ ላይ ምክክር እንደሚካሄድ አመልክተዋል፡፡

የአጀንዳ 2063 ትግበራን ጨምሮ በልዩ ልዩ አኅጉራዊ አጀንዳዎች ላይ ምክክር እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የኅብረቱ መቀመጫ ከመሆን ባለፈ ለተፈረሙ እና ለተጀመሩ አኅጉራዊ አጀንዳዎች ትግበራ ስሟ በተደጋጋሚ የሚነሣ የተግባር ምሳሌ መሆኗን አስረድተዋል።

እንደ ዕንቁ እየደመቀች በምትገኘው የአፍሪካውያን መዲና አዲስ አበባ የሚካሄደው አኅጉራዊ ጉባዔ የተሳካ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

Exit mobile version