አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለኢትዮጵያ ብሎም ለቀጣናው ዘላቂ ልማት መረጋገጥ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆን አስፈላጊ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በዛሬው ዕለት የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በጉባዔው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ አህጉራዊ ትስስርን እውን ለማድረግ አባል ሀገራት በሁሉም ዘርፍ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትስስርን ለማጠናከር በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝ ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡
ለአብነትም የአፍሪካ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ሀገራትን ሁለንተናዊ ትስስር ለማጠናከር በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ትስስሩን ሙሉ እና የተጠናከረ ማድረግ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ ለዚህም የተለያዩ የትስስርና የመዳረሻ አማራጮችን ማስፋት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በተለይም ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ መገኛ ለሆነችው ኢትዮጵያ ዘላቂ ዕድገት መረጋገጥ የባሕር በር ተጠቃሚነት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ሰላማዊ የትብብር መርሕን መሰረት በማድረግ ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፍትሃዊ የባሕር በር ተጠቃሚነት እውን መሆንም ለሀገሪቱ እድገት ብሎም ለቀጣናው ዘላቂ ልማት መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ

