አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘመን ተመልካች ብቻ ሳትሆን ዘርፉን የምትገነባ እና የምትመራ እንድትሆን ለማድረግ እየተሰራ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ ፖድ (Al UniPod) የፈጠራ ማዕከልን ስራ አስጀምረዋል።
ኢትዮጵያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘመን ተመልካች ብቻ ሳትሆን ዘርፉን የምትገነባ፣ አስተዋጽኦ የምታበረክትና የምትመራ እንዲሁም ወደፊት ለመራመድ አዲስ ምዕራፍ የምትከፍትበት መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ገልጸዋል።
ማዕከሉ በአፍሪካውያን ለአፍሪካ የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በመገንባት ለዓለም ማጋራት እንደሚያስችል ገልጸው÷ ይህም ብሔራዊ መሰረት የሚጣልበት ብቻ ሳይሆን ለአህጉሪቱ ያለንን ፍላጎትና ሕልም የምንገልጽበት ነው ብለዋል።
ዩኒፖድ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለምልክት ብቻ ሳይሆን የመዋቅራዊ እቅዳችን አካል ነው በማለት ጠቅሰው÷ በዘመኑና በኢንዱስትሪ ደረጃ ያሉ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሳሪያዎች እና መዋቅርን የማሸጋገር አቅም ባላቸው የተዋቀረ የፈጠራ ስራ ማዕከል መሆኑን አመልክተዋል።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሉዓላዊነት ተለዋዋጭ መልክ ያለው እና በድንበሮች የማይወሰን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ሉዓላዊነት ማን መረጃ አለው እና አልጎሪዝምን እየመራ ያለው ማነው ከሚለውና መረጃን የመቀመር አቅም ያለው ማነው ከሚለው ጋር የተሳሰረ እየሆነ ነው ብለዋል።
ዩኒፖድ ኢትዮጵያን ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ወደ ፈጣሪነት፣ ዓለም አቀፍ የዘርፉ ቁሶችን ከማላመድ የራሳችንን ዲዛይን ወደ ማድረግ፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ ተካፋይ ብቻ ከመሆን አቅጣጫውን ወደ መወሰን የሚያሸጋግራት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ዩኒፖድ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ከኢትዮጵያ ዲጂታል 2030 ጋር የሚናበብና የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳን ለማላቅ የሚያስችል እንደሆነም ጠቁመዋል።
ማዕከሉ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ቲምቡክቱ ኢንሼቲቭ በኩል በተደረገ ጠንካራ ትብብር እውን መሆኑ ተመላክቷል።
በለይኩን ዓለም

