አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን ለኢትዮጵያ ራስን ፈጽሞ መስጠት ምንጊዜም የማይጠፋ የሀሳብ እቶን እና የማይበርድ የመንፈስ ሙቀት መሆኑን ያስመሰክርንበት ነው አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ።
ፕሬዚዳንት ታዬ በማሕበራዊ ትስስር ገፃቸው÷ ለ89ኛው የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም ቀኑ ኢትዮጵያን ማፍቀርና መውደድ፣ ለኢትዮጵያ ራስን ፈጽሞ መስጠት ምንጊዜም የማይጠፋ የሀሳብ እቶን እና የማይበርድ የመንፈስ ሙቀት መሆኑን ያስመሰክርንበት ነው ብለዋል።
ራስን ለታላቅ ሀገራዊ ርዕይ አሳልፎ መስጠቱ በኢትዮጵያ የነበረ፣ ለአንድነቷና ለዕድገቷ በሚተጉ ዜጎቿ ዛሬም ሲገለጥ የምናየውና ነገ ደግሞ በኢትዮጵያዊነት ፍቅር ፀንቶ የሚኖር ሕያው ኃይል እና የማያቋርጥ ጥሪ መሆኑን አመልክተዋል።
የዘመናችን የዕውቀትና የሥራ አርበኞች ከፍ ያለውን ኢትዮጵያዊ ርዕይና ተስፋችንን ለማሻገር የትናንቱን የመስዋዕትነት ችቦ በጥበብ ፈላጊነት እና በሥራ ወዳድነት አስቀጥሉት ሲሉም አሳስበዋል።

