አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በነቀምቴ ከተማ በ30 ቢሊየን ብር ወጪ የሚገነባው የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ የችግሮች መፍቻ ቁልፍ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ የተቀናጀ የምግብ ኢንዱስትሪ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
ይህ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ማዕከል በቆሎን እና ሌሎች የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር ለአርሶ አደሩ የተሻለ ገቢ የሚያስገኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ለበርካታ ወጣቶች ሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ነው የገለጹት፡፡
የከተማዋ ተወላጅ የሆኑ ባለሃብቶች እና የዳያስፖራ አባላት በፓርኩ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ የከተማዋን ዕድገት እንዲያፋጥኑ ጥሪ አቅርበዋል።
ነቀምቴን መገንባት የሚቻለው በሥራ እና በልማት እንጂ በምሬት አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ሁሉም ለከተማው ብልጽግና የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
የቡሳ ጎኖፋን የመረዳዳት እና ራስን የመቻል እሴትን በማጎልበት ከልመና ወጥቶ በራስ ጥረት መበልጸግ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ከመናቆር ይልቅ ወደ ሥራ እና ወደ ጠንካራ አንድነት በመመለስ ለሀገር ግንባታ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በወለጋ ዞኖች ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በሚገባ በመጠቀም የተጀመረውን ሁለንተናዊ ልማት ማጠናከር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሲፈን መገርሳ

