Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ በትውልድ ቅብብሎሽ ሀገር ያጸኑ ጀግኖች ምድር ናት – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በትውልድ ቅብብሎሽ ሀገር ያጸኑ የበርካታ ጀግኖች ምድር ናት አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በተገኙበት የመከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች እዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እየተከበረ ይገኛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ የልዩ ዘመቻዎች እዝ ባለፉት 65 ዓመታት በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ የማይበገር ጽናት ይዞ ኢትዮጵያን ያኮራ ጀብዱ ፈጽሟል ብለዋል።

እዙ በመከላከያ ሪፎርም አማካኝነት አየር ወለድ፣ ኮማንዶ እና ልዩ የጸረ ሽብር ኃይልን በመያዝ በአደረጃጀት፣ በሠው ኃይልና በትጥቅ ዘመኑን በዋጀ መልኩ ተዋቅሮ በየትኛውም ጊዜና በማንኛውም ሁኔታ ግዳጁን በብቃት ለመፈጸም በአስተማማኝ ቁመና ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

65ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር የገነባውን ዘመናዊ ወታደራዊ አቅም፣ የሰው ኃይል ዝግጁነትና የታክቲክ ብቃት ለሕዝብ ይፋ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡

በተለይም ዛሬ የቀረበው የተቀናጀ የውሃ ላይ ልምምድ፣ የአየር ወለድና የኮማንዶ አባላት በቅንጅት ያሳዩት ልዩ ልዩ ወታደራዊ ክህሎት የሠራዊቱን ከፍተኛ ብቃት ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

Exit mobile version