Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የቀይ ቦኔት ክብር የገባውና ለሀገር ባንዴራ፣ ክብርና ነጻነት የሚሰዋ ሠራዊት ተገንብቷል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀይ ቦኔት ክብር የገባውና ለሀገር ባንዴራ፣ ክብርና ነጻነት ራሱን የሚሰዋ እንዲሁም ለቀጣናው ሀገራት መከታ የሆነ ሠራዊት ተገንብቷል አሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
የመከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች እዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በተገኙበት በሐዋሳ በድምቀት ተከብሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ÷ የዛሬ አየር ወለዶች ከእናት ከአባታቸው፣ ከኢትዮጵያ ሀገራቸው እንዲሁም ከአየር የተወለዱ የኢትዮጵያ ልዩ ስጦታዎች ናቸው ብለዋል።
የኤሊት ፎርስ አባላት ውጊያ የሚያስቀሩና የሚጨርሱ የአፍሪካ የነጻነት ቀንዲል የሆነውን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ አላማችንን በድል የሚያውለበልቡ ጀግኖች እንደሆኑ አውስተዋል፡፡
አባላቱ የቀይ ቦኔት ክብር የገባቸው፣ ለሀገር ባንዴራ፣ ክብርና ነጻነት ራሳቸውን የሚሰው እንዲሁም ለቀጣናው ሀገራት መከታና አለኝታ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአዕምሮም ሆነ በአካል የበለጸገ፣ ቴክኖሎጂን በሚገባ የሚያጫውትና የሚጠቀም፣ ውጊያን የሚሰራና የሚጨርስ ሰራዊት መገንባቷን አመልክተዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ነጻነትና የአፍሪካን ሰላም ዛሬም እንደትናንቱ የሚያስከብር አስተማማኝ ሃይል መሆኑን አብስረዋል፡፡
የእኛ ዝግጅት በድፍን አፍሪካ ሰላምና ብልጽግናን ለማረጋገጥ፣ በቀጣናችን ላሉ ሀገራት አለኝታ፣ መከታ፣ ጋሻ ለመሆን ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ከሶማሌ ጫፍ እስከ ምጽዋ ጫፍ በባሕር የሚያጋጥሙ ሽብሮችን፣ ወንድም ሕዝቦችን ደግፈን ሽብርን ለማስቀረት እና ልማት ብልጽግናን በቀጣናችን ለማረጋገጥ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣናው በቂ የሆነ ኤሊት ፎርስ ገንብተናል ነው ያሉት፡፡
ላባችንን አንጠፍጥፈን፣ ደማችንን አፍስሰን፣ አጥንታችንን ከስክሰን ኢትዮጵያን እንገነባለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ ኢትዮጵያ በልጆቿ ላብ ትሰራለች፤ በልጆቿ አጥንት እና ደም ትጸናለች ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብልጽግና፣ የኢትዮጵያ የአፍሪካ መሪነትና ምሳሌነት ይረጋገጣል፣ ለልጆቻችን ድህነትን ታሪክ አድርጋ ለመላው አፍሪካ ኩራት የምትሆን ሀገር እናስረክባለን ሲሉም በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ዜጎች የሃዋሳን ብርሃን፣ የሕዝቡን ፍቅር እና ታሪካዊ ማንነት በቅዳሜ እና እሑድ እየመጡ እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ
Exit mobile version