አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የብላቴ በረሃ የሰው ልጅ በርትቶ ከሰራ ምን ሊያመጣ እንደሚችል ያመላክታል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብላቴ ወንዝ አካባቢ የተከናወነ የፍራፍሬ ልማትን የጎበኙ ሲሆን÷ የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ወደ ብላቴ መምጣታቸውን አስታውሰው÷ በወቅቱ አካባቢው በረሃና ምንም ነገር እንዳልነበር አመልክተዋል።
አሁን ላይ ግን ብርቱካን፣ ሎሚ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ሸንኮራገዳና አቮካዶን ጨምሮ ብዙ ፍራፍሬዎች እየተመረቱ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ በመቶ ሄክታሮች በመስኖ እየታረሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የብላቴ በረሃ የሰው ልጅ በርትቶ ከሰራ ምን ሊያመጣ እንደሚችል ያመላክታል ሲሉም ገልጸዋል።
ሲዳማ ክልል በዚህ ዓመት 15 ሚሊየን ዶሮ እያመረተ መሆኑን ገልጸው÷ የዛሬ ሦስት ዓመት 4 ሚሊየን አካባቢ እንደነበርና በብዙ እጥፍ እንዳደገ አስረድተዋል።
በዚህም ሌማት እየተስፋፋ መሆኑን፣ የፍራፍሬ ምርት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱን፣ ከተሞች እየተለወጡ መሆናቸውን እንዲሁም ኢንዱስትሪዎች ኢንዱስትሪ ብቻ ሳይሆን ኤክስፖርት ወደ ማድረግ እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል።
ይህ ሁሉ ሲደመር ኢትዮጵያ ከነበረችበት የልመናና የታሪክ ድህነት አስቀርተን ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።
በሁሉም መስክ አስተማማኝ ጅማሮዎች መኖራቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ መስፋፋት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በአንድ መስክ ያለ ውጤት ሁሉም ችግር አይፈታም በማለት ገልጸው÷ በግብርናው፣ በኢንዱስትሪው፣ በከተማው፣ በሌማቱ፣ በገጠር ኮሪደሩ የጀመርናቸው ስራዎች ሲተሳሰሩ የምናስባትን ኢትዮጵያ ለመፍጠር በእጅጉ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በአድማሱ አራጋው
👉ለፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎች የፋና ዲጂታል አድራሻዎችን ከአስተያየት መስጫ ሳጥን ያግኙ፡-

