አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መገናኛ ብዙሃን በነፃነት እንዲሰሩ የሚያስችል አውድ ለመፍጠር በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል አሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፡፡
አቶ አደም ፋራህ በፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተገኝተው የተቋሙን የሥራ እንቅስቃሴና ያከናወናቸውን የማሻሻያ ተግባራት ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸው ምቹ የስራ ከባቢን ከመፍጠርና ተወዳዳሪነትን ከማላቅ አንጻር በርካታ ስራዎች መስራታቸውን መመልከታቸውን ገልጸው፥ ይህም ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽንን ይበልጥ ጠንካራና ተወዳዳሪ እንዲሆን ያስችለዋል ነው ያሉት፡፡
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ የሚዲያ ታሪክ ጉልህ አሻራ ያሳረፈ ተቋም መሆኑን አንስተው፥ በአሁኑ ወቅትም ለዘመኑ የመገናኛ ብዙሃን ውድድር የሚያግዙ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ተቋሙ ዘመናዊነትን ከህዝብ አመኔታ ጋር ያቀናጀ በመሆኑ ተልዕኮውን በተሳለጠ መንገድ እንዲወጣ የሚያስችለው ቁመና ላይ እንዲገኝ አግዞታል ብለዋል፡፡
ከለውጡ ወዲህ መገናኛ ብዙሃንን በተለያዩ ተቋማት የተከናወኑ የማሻሻያ ተግባራት አካል በማድረግ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ነው የገለጹት፡፡
ከዚህ ቀደም መገናኛ ብዙሃን በነፃነት እንዳይሰሩ የሚገድቡ የህግ ማዕቀፎችን በማሻሻል በነፃነት እንዲሰሩ የሚያስችላቸውን አውድ ለመፍጠር ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽንም ከለውጡ ወዲህ የተገኙ የመገናኛ ብዙሃን ነፃነትን በአግባቡ እየተጠቀመ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በሔብሮን ዋልታው

