አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ባለ ጉዳዮች ጊዜያቸውና ገንዘባቸው ሳይባክን ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏል አለ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ ወሰንየለህ ስምኦን ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ማዕከሉ ወደ ሥራ ከገባ ወዲህ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል፡፡
ከዚህ ቀደም ዜጎች አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተለያዩ ተቋማት በመሄድ ጊዜያቸው እና ገንዘባቸው ይባክን እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
አሁን ላይ ግን ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ቦታ ማግኘት በመቻላቸው ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን እና ጉልበታቸውን በመቆጠብ በአጭር ጊዜ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የአገልግሎት ክፍያ ሥርዓቱ በዲጂታል መሆኑ አገልግሎቱ ቀልጣፋ እንዲሆን ማድረጉን ጠቁመው÷ ብልሹ አሰራርን በመከላል ረገድ ያለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
በማዕከሉ 17 ተቋማት 38 አገልግሎቶችን እየሰጡ ይገኛሉ ያሉት ሃላፊው÷ በቀጣይ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሉ ሥራ ከጀመረ ወዲህ እስካሁን 25 ሺህ 800 ተገልጋዮች አገልግሎት ማግኘታቸውን አስረድተዋል፡፡
በክልሉ በሚገኙ ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ÷ለዚህም የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን አመልክተዋል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ

