Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የአዘርባጃን ጉብኝትና አዳዲስ አጋርነቶች…

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዘርባጃን ያደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ኢትዮጵያ አዳዲስ ትብብርና አጋርነቶችን ለማጠናከር እንደምትሰራ የሚያሳይ ነው አሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፡፡

ሚኒስትሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና የልዑካን ቡድናቸውን የአዘርባጃን ጉብኝት አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷ ኢትዮጵያ ካደጉ ሀገራት ጋር ከምታደርገው ግንኙነት ባሻገር ከሌሎች ሀገራት ጋር አዳዲስ ትብብሮችን የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባላት ቀጣናዊና አህጉራዊ ተጽዕኖ በርካታ ሀገራት ከአፍሪካ ጋር ለሚያደርጉት ግንኙነት የሚመርጧት ሀገር መሆኗን የገለጹት ሚኒስትሩ፥ በኢኮኖሚ ማሻሻያው ማዕቀፍ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች የኢንቨስትመንት ስበት እየጨመረ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

በዚህም መሰረት አዘርባጃን በአፍሪካ በንግድና ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ባላት ፍላጎት ኢትዮጵያን ቀዳሚ ምርጫዋ አድርጋለች ነው ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ልዑካቸው በአዘርባጃን ያደረጉት ጉብኝት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች የትኞቹ እንደሆኑ የሚያመላክት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከፍ ያለ ተጽዕኖ ካላቸው የተወሰኑ ሀገራት ጋር ብቻ ታደርግ የነበረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በማስፋት በተለይም አግባብነት ያለው ልምድና ተሞክሮ ከሚገኝባቸው ሀገራት ጋር አዳዲስ ትብብሮችን ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት አስረድተዋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት አዘርባጃን የራሷን የቴክኖሎጂ አቅም ከውጭው ጋር በማጣመር ያላትን የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ኃይል ጥቅም ላይ ያዋለችበት መንገድ ልምድ የተገኘበት እንደነበር አንስተዋል፡፡

ሀገሪቱ በአንድ የኢኮኖሚ ምንጭ ላይ ብቻ ከመመርኮዝ ይልቅ ብዝሃ ኢኮኖሚን ተግባራዊ በማድረግ እድገቷን እያፋጠነች መሆኗን ጠቅሰው፥ ይህም ለኢትዮጵያ ትምህርት ሰጪ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

Exit mobile version