አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ130ኛው የዐድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
እንኳን ለ130ኛው የዐድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ።
የዐድዋ ድል የኢትዮጵያውያንን የማይቀየር ዐቋምና ዐቅም ያሳየ ድል ነው። ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም፣ ነጻነትና ሉዓላዊነት ላይ የማይቀየር ዐቋም አላቸው።
ይሄንን ዐቋማቸውን በጽኑ መሠረት ላይ ለመትከል ደግሞ ሁሉንም አቅማቸውን ይጠቀማሉ።
ሥርዓታትና መሪዎች ሊቀየሩ ይችላሉ፤ በአንዳንድ ጉዳዮች ልዩነቶች ይኖሯቸው ይሆናል፤ ስለ ሀገራቸው ያላቸው ዐቋምና ለሀገራቸው የሚያወጡት አቆም ግን አይቀየርም።
ወደ ዐድዋ የዘመቱ ጀግኖቻችን ሁሉ በሁሉም ነገር የተስማሙ አይደሉም። አንድ ዓላማ ነበራቸው እንጂ አንድ ዓይነት አልነበሩም። አንድ ሀገር ነበራቸው እንጂ አንድ ባህልና እምነት አልነበራቸውም።
በዚያ ጊዜ ሀገራቸውን ከድተው ከጠላት ጋር ያበሩ ባንዳዎች ነበሩ። ለጊዜያዊ ጥቅም ሲሉ ዘላቂ የሀገራቸውን ጥቅም የሸጡ ምንደኞችም ነበሩ። ከባዳ ጋር ወግነው ወገናቸውን ያስማሙ ደላሎችም ነበሩ።
ጀግኖች እናቶቻችን እና አባቶቻችን የተዋጉት ከወራሪው የጣሊያን ጦር ጋር ብቻ አልነበረም።
ከምንደኞች፣ ከባንዳዎች እና ከሀገር ደላሎች ጭምር እንጂ። ዐርበኝነት ማለት ባዳና ባንዳን ማሸነፍ ማለት ነው። ዐርበኝነት ማለት ለሀገር ጥቅም ሲባል የግል ጥቅምን ማሸነፍ ማለት ነው። ዐርበኝነት ማለት ለሀገር ክብር ሲባል የራስን ክብር መሠዋት ነው።
የዐድዋ ድል በዓል እነዚህን ሁሉ የምናስታውስበት ነው። የዐድዋ ድል በዓል የኢትዮጵያውያንን ዐቅምና አቋም እንደገለጠው ሁሉ ዛሬም በጸና አቋም፣ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዐቅም የምንገልጥበት ጊዜ ነው።
በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን እና በዲጂታል ሀገራችን ያላትን ዐቅም መግለጥ አለብን። የዐድዋን ድል በሁሉም ዘርፍ ለመድገም፣ የኢትዮጵያ ዐቅም ጽኑ መሠረት ሊኖረው ይገባል።
ሀገርን ዐቅም ያሳድጋታል፤ ዐቅም ይገነባታል። ሀገርን ዐቅም ይሠራታል። ዐቋም ያጸናታል። ሀገርን ዐቅም ያራምዳታል፤ ዐቋም ያሻግራታል።
የዐድዋ ድል በዓላችን የኢትዮጵያን ዐቅም ይበልጥ የምንገነባበትና የኢትዮጵያውያንን ዐቋም ይበልጥ የምናጸናበት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
የካቲት 22 ቀን 2018 ዓ.ም

