Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጀግኖች አባቶቻችን የተዋጉት ከጣሊያን ጦር ጋር ብቻ ሳይሆን ከባንዳዎችና ምንደኞች ጭምር ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ130ኛው የዐድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው÷ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም፣ ነጻነትና ሉዓላዊነት ላይ የማይቀየር ዐቋም አላቸው ብለዋል።

ሥርዓታትና መሪዎች ሊቀየሩ ይችላሉ፤ በአንዳንድ ጉዳዮች ልዩነቶች ይኖሯቸው ይሆናል፤ ስለ ሀገራቸው ያላቸው ዐቋምና ለሀገራቸው የሚያወጡት አቆም ግን አይቀየርም ነው ያሉት።

ወደ ዐድዋ የዘመቱ ጀግኖቻችን ሁሉ አንድ ዓላማ ነበራቸው እንጂ አንድ ዓይነት አልነበሩም ፤ አንድ ሀገር ነበራቸው እንጂ አንድ ባህልና እምነት አልነበራቸውም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷፡፡

በዚያ ጊዜ ሀገራቸውን ከድተው ከጠላት ጋር ያበሩ ባንዳዎች ፣ለጊዜያዊ ጥቅም ሲሉ ዘላቂ የሀገራቸውን ጥቅም የሸጡ ምንደኞችና ከባዳ ጋር ወግነው ወገናቸውን ያስማሙ ደላሎች እንደነበሩም አስረድተዋል፡፡

ጀግኖች እናቶቻችን እና አባቶቻችን የተዋጉት ከወራሪው የጣልያን ጦር ጋር ብቻ ሳይሆን ከምንደኞች፣ ከባንዳዎች እና ከሀገር ደላሎች ጭምር እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

ዐርበኝነት ማለት ባዳና ባንዳን ማሸነፍ፤ ዐርበኝነት ማለት ለሀገር ጥቅም ሲባል የግል ጥቅምን ማሸነፍ ፤ ዐርበኝነት ማለት ለሀገር ክብር ሲባል የራስን ክብር መሠዋት እንደሆነም አውስተዋል፡፡

የዐድዋ ድል በዓል እነዚህን ሁሉ የምናስታውስበት ነው፤ የዐድዋ ድል በዓል የኢትዮጵያውያንን ዐቅምና አቋም እንደገለጠው ሁሉ ዛሬም በጸና አቋም፣ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዐቅም የምንገልጥበት ጊዜ ነው ብለዋል።

በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና ዲጂታል ሀገራችን ያላትን ዐቅም መግለጥ አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የዐድዋን ድል በሁሉም ዘርፍ ለመድገም የኢትዮጵያ ዐቅም ጽኑ መሠረት ሊኖረው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

Exit mobile version