Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያውያን አልፎ መላው ጥቁር ሕዝቦችን ያኮራ ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያውያን አልፎ መላው ጥቁር ሕዝቦችን ያኮራ ታሪካዊ ድል ነው አሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ።
130ኛው የዓድዋ ድል በዓል “ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበዓሉ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት÷ የዓድዋ ድል የጸረ ቅኝ ግዛት ቀንበር ከጥቁር ሕዝቦች ላይ እንዲሰባበር መንገድ የከፈተ የተጋድሎ ታሪክ ነው።
የዓድዋ ድል ጥቁሮች ታሪክ መስራት የማይችሉ ናቸው የሚለውን የፋሺሽቶች አስተሳሰብ የሰበረ ኃያል ድል ነው በማለት ገልጸው÷ ኢትዮጵያውያን በፈረሶቻቸው፣ በጦርና ጋሻዎቻቸው፣ በተወሰነ ኋላቀር የጦር መሳሪያዎቻቸው ከምንም በላይ ደግሞ በአይበገሬነታቸው ጠላትን ያሳፈሩበት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጀግኖች የማይበገሩ ከሕዝብ የአርበኝነት ታሪክ ቅብብሎሽ የተፈጠሩ የቀድሞ ትውልድ ወራሾች ናቸው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ÷ አርበኝነት፣ ጀግንነትና በራስ የመተማመን ባህላችን ከዓድዋ ድል በፊት የነበረ፣ በዓድዋ ድል የተደገመ ብሎም እስከዛሬ የተላለፈልን ታሪካችን ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሶስና አለማየሁ
Exit mobile version