አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ በመላው አፍሪካ እና ጥቁር ሕዝብ ላይ ጨልሞ በነበረ ሰማይ ፀሐይ የፈነጠቀበት ቀን ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ኢትዮጵያ ድንበሯን ገፍቶ ሉዓላዊነቷን እና የሕዝቧን ነጻነት የደፈረውን የወራሪውን ጦር በዓድዋ ተራሮች ድል የነሳችበትና ለ3 ሺህ ዓመታት ያልተደፈረውን ስልጣኔዋን ያጸናችበት ቀኗ ነው ብለዋል፡፡
ተከብረን የምንኖርባትን ኢትዮጵያን ከድንቅ ስልጣኔ እና ታሪክ ጋር ከነታላቅ ክብሯ በደም መስዋዕትነት ላስረከቡን አባቶቻችን ክብር ይገባቸዋልም ነው ያሉት፡፡
ዛሬ የምንኖር ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን እና እናቶቻችን ሞተው ያቆሙልንን ሀገር በአንድነት እና በፍቅር በመኖር ልናስቀጥል ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
ከእነሱ ተምረን ድህነትን፣ መከፋፍልን እና ኋላ ቀር አስተሳሰብን አሻፈረኝ በማለት ኢትዮጵያን ወደ ብልጽና ልናሻግር ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ ከሆነችው በላይ ታላቅ የምትሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ሲሉም አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡

