አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የዘመናችን ጀግና የነውጥ ጩኸትን የሚዋጅ ሳይሆን የሀገር ፍቅር፣ የመቻቻል፣ የዕውቀት፣ የጥበብና አብሮ የማደግ ድምጽን የሚያጎላ ነው አሉ።
130ኛው የዓድዋ ድል በዓል “ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።
ፕሬዚዳንት ታዬ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት÷ የዓድዋ አስተምሮት ኢትዮጵያዊነትን ሲያገዝፍ የቡድን ዕሳቤን በአግባቡ ከርክሞ የሚይዝ ነው።
ዓድዋ ጸብ አጫሪዎችንና መከፋፈልን ልማድ ያደረጉትን ያጨምታል፣ ሌብነትን፣ ውስልትናንና ሐኬትን ይንቃል፤ የዘመኑ ዓድዋ ቁልፍ ጉዳይም ይኽ ነው ብለዋል።
ዓድዋ ለፖለቲካ አስተምህሮት የሚሰጠን ትልቅ ትምህርት ምንጊዜም የግጭትን ግለት ለሚሹ፣ ለጦርነት ትርክት ብቻ አፋቸው ለሚላወስና ሰላምን በመዝገበ ልቦናቸው ላልከተቡ ወገኖች ሁሉ ግብረ ገብነትን የሚያስተምር ታላቅ መካነ ዕውቀት እንደሆነ አመልክተዋል።
ዓድዋን ስናስብ በአዕምሯችን የሚመላለሰው ጀግንነት ነው፤ ጀግንነት ደግሞ ሰላምን ማጽናት፣ ሕዝብን መጥቀምና ሀገርን ማበልጸግ ነው ብለዋል።
ስለሆነም የዘመናችን ጀግና የነውጥ ጩኸትን የሚዋጅ ሳይሆን የሀገር ፍቅር፣ የመቻቻል፣ የዕውቀት፣ የጥበብና አብሮ የማደግ ድምጽን የሚያጎላ ነው ሲሉም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያዊነት በዓድዋ ሚዛን ሲመዘን ደግሞ ህይወትን በመለገስ የጸና፣ በላብ የጠነከረ፣ በዕውቀት፣ በትዕግስትና በአርቆ አስተዋይነት የሚለመልም ህያው ማንነት እንደሆነ አብራርተዋል።
በአድማሱ አራጋው

