አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮችና የልዑካን ቡድን መሪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ሚኒስትሯ ከኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዚምባብዌ፣ ዛምቢያ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ቦትስዋና፣ ሩዋንዳ፣ ኮንጎ፣ ካሜሩን፣ ማሊና አልጄሪያ የመከላከያ ሚኒስትሮች ጋር ነው የመከሩት፡፡
በውይይቱ ወቅት ቀደም ሲል በሀገራቱ መካከል የተፈረሙ የትብብር ስምምነቶች ያሉበት የአፈጻጸም ደረጃ በጥልቀት መገምገሙ ተመላክቷል፡፡
አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የዓድዋ ድል አሁን ላይ አፍሪካ የተደቀኑባትን ወቅታዊ የፀጥታና የደኅንነት ስጋቶች በጋራ ለመመከት እንደ ትልቅ የመንፈስ ምንጭና የትብብር ማዕቀፍ ሊያገለግል ይገባል።
የአህጉሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ የሚያስችል የጋራ ግንዛቤ በመያዝ በአንድነት እና በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመድረኩ በተለይም በወታደራዊ ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሥልጠና እና በልምድ ልውውጥ መስኮች በጋራ ለመሥራት መግባባት ላይ መደረሱ ተመላክቷል፡፡
ሽብርተኝነትንና ድንበር ተሻጋሪ የጸጥታ ስጋቶችን በጋራ ለመከላከል የሚያስችሉ ስልታዊ የትብብር አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል፡፡
የአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ለአህጉራዊ ሰላምና መረጋጋት እያበረከተች ያለውን ቀዳሚና የማይተካ ሚና አድንቀዋል።
የጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነውን የዓድዋ ድል በዓልን በኢትዮጵያ ተገኝተው ከወንድሞቻቸው ጋር በጋራ በማክበራቸው ጥልቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በጋራ የመከላከል አቅም ግንባታ ላይ በቁርጠኝነት ለመሥራት ያላቸውን ፅኑ ፍላጎት አረጋግጠዋል።
ይህ የሁለትዮሽ ውይይት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት ከማሳደጉም ባለፈ የአህጉሪቱን የጋራ ደኅንነትና ትስስር ለማረጋገጥ የሚደረገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ይበልጥ እንደሚያጠናክር ተጠቅሷል፡፡
ውይይቱ 130ኛውን የዓድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ኮንፈረንስ ጎን ለጎን ነው የተካሄደው፡፡
በመላኩ ገድፍ

