አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የምስራቅ ሐረርጌ ዞን የተለያዩ ድንቅ ተፈጥሮ እና ማዕድናት ሃብት መገኛ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ በድሬዳዋ አስተዳደር፣ በሐረሪ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ ዞን የተለያዩ የልማት ስራዎችን እና የቱሪስት መዳረሻዎችን ጎብኝተዋል።
ጉብኝታቸውን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን መልካ በሎ ወረዳ ውስጥ የሚገኘውን ናሲኦል ዋሻ 500 ሜትር በእግር ተጉዘው የዋሻውን ድንቅ የተፈጥሮ ገጽታ መመልከታቸውን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ገና ታውቅ ተዝቆ የማያልቅ ሃብት እንዳላት የናሲኦል ዋሻ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
የናሲኦል ዋሻ የላይኛው ክፍል እምነበረድ የሚመስሉ እና የተለያየ ቀለም ያላቸው ሹል ድንጋዮች መኖራቸውን በመጥቀስ÷ የዋሻውን ተፈጥሯዊ ገፅታ ለመግለፅ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ብዙ ዋሻዎች፣ ፍል ውሃዎች፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳት እንዲሁም እንደ ማርቭል እና ግራናይት የመሳሰሉ ማዕድናት መገኛ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ዞኑ መሰረተ ልማቶች ቢሟሉለት እነዚህን የተፈጥሮ ጸጋዎች በማልማት የአካባቢውን ማህበረሰብ የበለጠ ተጠቃሚ ማድረግ ይችላል ነው ያሉት፡፡
በተመሳሳይ በሐረሪ ክልል ሐረር ከተማ ባደረጉት ጉብኝት የጁገል ግንብ ባማረ ሁኔት ተሻሽሎ መገንባቱን ጠቅሰው፤ ሐረር ወደ ነበረ ስሟ፣ ክብሯ እና ገናናቷ የመመለስ ጉዞ እንደጀመረች ተመልክቻለሁ ብለዋል፡፡
የሐረሪ ህዝብ የተለየ ሀብት ሳይኖረው ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር ከተማዋን ለማስዋብ ያደረገውን ጥረት አድንቀዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ

