አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ብሔራዊ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ስትራቴጂ ይፋ አድርገዋል።
ከፈረንጆቹ 2026 እስከ 2030 ተግባራዊ የሚደረገው ስትራቴጂ በመንግሥት አገልግሎቶች ውስጥ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ስትራቴጂውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት፥ ፈጠራን ለማጎልበት፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን ለማሻሻልና የሀገሪቱን ዲጂታል ለውጥ ለመደገፍ እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ባለንበት ፈጣን የቴክኖሎጂ ለውጥ ዘመን የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራ ምላሽ መሆኑን ገልጸው፥ የግብርና፣ የማዕድን፣ የጤና፣ የፋይናንስ እና ትምህርት ዘርፎችን ለማሳደግ ይረዳል ነው ያሉት፡፡
የሰው ሰራሽ አስተውሎት እውቀትን ለማዳበር የሚያግዙ ልዩ የምርምር ማዕከላትን ለማቋቋም ታቅዷል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ቴክኖሎጂውን ለሚጠቀሙ የንግድ ተቋማት ማበረታቻዎችን ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ታቴንዳ ማቬቴራ በበኩላቸው፥ በሀገሪቱ የዲጂታል መሠረተ ልማት መሻሻሎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለይም የመንግስት ሰራተኞች ሰው ሰራሽ አስተውሎትን እንዲጠቀሙ ስልጠና እየተሰጠ ነው ማለታቸውን ቪዮሪ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።
በርካታ ሀገራት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ትኩረት በማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ ከዓመታት አስቀድማ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን በማቋቋም በርካታ ስራዎችን እየሰራች ትገኛለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የእድገት ምሰሶ አድርጋ ከያዘቻቸው አምስት ጉዳዮች መካከል ቴክኖሎጂ አንዱ መሆኑን ገልጸው፥ በዓለም 2ኛ የሆነውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲን ለመገንባት እየሰራች ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡
በዮናስ ጌትነት

