አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 1 ሺህ 447ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል የዒድ ሶላት ሥነ ሥርዓት በሀገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት ተከናውኖ ተጠናቅቋል አለ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ።
ተቋሙ እንዳስታወቀው÷ የዒድ ሶላት እና የተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ጋር በመቀናጀት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ሰፊ የሰው ኃይል በማሰማራት ተገቢውን የፀጥታ ሥራ በማከናወን ኃላፊነቱን በሚገባ ተወጥቷል።
ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የተጠናከረ ጥበቃ በማከናወን በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታቸው በብቃት የተወጡ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማትን አመራሮችና አባላትን አመስግኗል።
በተመሳሳይ ለፀጥታና ደኅንነት አካላት አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ላደረገው መላው ህዝብ፣ ለሃይማኖት አባቶች፣ ለበዓሉ አስተባባሪዎች፣ ለእምነቱ ተከታዮች እና ለወጣቶች ምስጋና ያቀረበው፤ የህብረተሰቡ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል፡፡

