Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በባሕር ዳር ከተማ እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ለኢኮኖሚ ዕድገታችን የጎላ ፋይዳ ይኖራቸዋል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በባሕር ዳር ከተማ እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የከተማዋን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ለኢኮኖሚ ዕድገታችን የጎላ ፋይዳ ይኖራቸዋል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ ዛሬ በባሕር ዳር የከተማዋን የቱሪዝም እና የኢኮኖሚ ማዕከልነት ይበልጥ የሚያጎሉና ግንባታቸው እየተፋጠኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት፣ የመንገድ መሰረተ ልማት እና የአየር መንገድ ፕሮጀክቶችን ተመልክተናል ብለዋል።

የከተማዋን ውበት እና የትራፊክ ፍሰት ለማሳለጥ እየተገነቡ የሚገኙ የከተማ ኮሪደር እና የመንገድ ልማት ሥራዎች በጥሩ አፈፃፀም ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

ከአሮጌው የዓባይ ድልድይ እስከ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የሚደርሰው አዲሱ የኮሪደር ልማት በአበረታች ጉዞ ላይ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በከተማዋ እየተገነባ የሚገኘው ከገብርኤል እስከ ምድረ ገነት አስፓልት መንገድ ግንባታም ተጠናቅቋል ብለዋል።

ከሃኒ ጋርደን እስከ ወረብ ድረስ ያለው የአዲሱ የዓባይ ድልድይ መዳረሻ አስፓልት ስራም ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ተመልክተናል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድ በባሕር ዳር እያከናወናቸው ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ማየታቸውን ገልጸው÷ በየካቲት 2016 ዓ.ም የተጀመረው የባሕር ዳር የአብራሪዎች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ግዙፍ ፕሮጀክት ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ማሰልጠኛው ዘመናዊ የመማሪያ ክፍሎች፣ የአሠልጣኞችና የተማሪዎች መኖሪያ ህንፃዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችንና አረንጓዴ ውብ ምድረ ግቢን በውስጡ ያካተተ መሆኑን አመላክተዋል።

በባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ ፕሮጀክት እየተገነባ የሚገኘው አዲሱ ተርሚናል ግንባታው ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህ ተርሚናል በሰዓት እስከ 1 ሺህ መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል ብለዋል።

እነዚህ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የከተማዋን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ለኢኮኖሚ ዕድገታችን የጎላ ፋይዳ ይኖራቸዋል ሲሉም ገልጸዋል።

Exit mobile version