አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተፈጥሮ ጸጋና ውበት ማሳየት መቻል ለእኛ እንደ ትልቅ ዕድል የሚወሰድ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ’ገበታ ለትውልድ’ ውጥን አካል በሆነው ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ’ ምረቃ መርሐ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት÷ በአፋር ክልል ከአፍዴራ እስከ ኤርታሌ እጅግ የሚያስደንቅ ውበት አለ።
በአፋር ክልል በርካታ ቦታዎች ፍል ውሃዎች ሲፈልቁ የሚታይበት መሆኑን አንስተው÷ ይህንን ክልል መጠነኛ ኢንቨስትመንት በማድረግ ወርቁን ለማፈስ የሚያስችል ዕድል ለልጆቻችን መስጠት እንችላለን ብለዋል።
እንዲህ ያለውን ስራ መስራት ዓይን መግለጥ፣ የተፈጥሮ ጸጋና ውበት ማሳየት መቻል ለእኛ እንደ ትልቅ ዕድል የሚወሰድ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
አፋሮች ስለትጋትና ብርታት ከሚናገሯቸው ንግግሮች መካከል አንዱ “ዕድል ያንቀላፉ ሰዎችን አትቀሰቅስም” ይላሉ በማለት ገልጸው÷ እዚህ ቦታ ላይ ለረጅም ጊዜ ዕድል ስትዞር ነበር ብለዋል።
ይህ ጉዳይ መሰራት የነበረበት የዛሬ 50 እና 60 ዓመት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ አፋር ውስጥ በርካታ ቦታዎች መሰል ስራዎች እንደሚያስፈልግና የግል ዘርፍና የክልሉ አመራርን በንቃት በማሳተፍ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአፋር ክልል ውብ ተፈጥሮ እና ደጋግ ሕዝብ የጎብኚዎች ቆይታ እንዲራዘም ማድረግ የሚያስችል አቅም እንዳለው አመልክተዋል።
ይህ እንዲሆን ጨለምተኝነት፣ አይቻልም እና አይሳካም ከሚል ሐሳብ በመውጣት አሁን ባለ ሁኔታ ባለመታሰር፣ ከዚያ አልቆ እና አሻግሮ ማየት ሲቻል የምናስበውን የበለጸገች ኢትዮጵያ ለማየት እና ለልጆቻችን ለማስረከብ እንችላለንም ነው ያሉት።
በዚህ ስፍራ ያልተዳሰሰ፣ ያልተደረሰትና የተደበቀ ብዙ ሃብት ሊኖር እንደሚችል ጠቅሰው÷ በአካባቢው ያለው ውሃ፣ ድንጋዮች፣ የአትክልት ዓይነቶች ተጨማሪ ምርምርና ጥናት ቢደረግባቸው አዳዲስ ሃብት ሊወጣባቸው እንደሚችልም ጠቁመዋል።
በዮናስ ጌትነት

