አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለውጥ የሚመጣው ችግርንና መከራን ረግጦ፥ አሻግሮ በማየትና በመትጋት ብቻ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንትናው ዕለት የገበታ ለትውልድ ውጥን አካል የሆነውን ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ’ ባስመረቁበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ ጨለምተኛ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ባሉበት ሁሉ ያማረ ውጤት አይመጣም ከመጣም የዘገየ ይሆናል ብለዋል።
ብዙ መልካም አሳቢዎች ቢኖሩም የተበላሸ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች እንደሚቀላቀሉ ገልጸው፥ አንድ የተበላሸ ነገር የበዛውን መልካም ነገር እንደሚያበላሸው ተናግረዋል።
እነዚህ ሰዎች ስለ ችግር በማውራትና በመተንተን የሚታለፍ ይመስላቸዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለውጥ የሚመጣው ችግርንና መከራን፥ ረግጦ አሻግሮ በማየትና በመትጋት ብቻ ነው ብለዋል።
ጨለምተኝነት ትውልድ እንደሚገድል፣ ሀገርን እንደሚያዘገይና ለማኝ እንደሚያደርግ አንስተው፥ ከጨመልምተኝነትና ከአይሳካም አስተሳሰብ መውጣት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ይህ አካባቢ ከ2 እና 3 ዓመታት በፊት መንገድ ያልነበረበትና አሁን ያለውን መልክና ቅርጽ ይይዛል ተብሎ ሊታመን የማይችል እንደነበር አስታውሰው፥ ነገር ግን በተከታታይ ጥረት በምንም መስፈርት ሊናቅ የማይችል መልካም ዘር ተዘርቷል ነው ያሉት።
መልካም ጅማሮ የታየ ቢሆንም አሁንም አፋር ውስጥ መሰል ስራዎች እንደሚያስፈልጉ ገልጸው፥ አረሙን ለማጥፋትና ዘሩን ለማብዛት ብዙ ስራ እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።
እንዲህ ያለውን ተፈጥሮ በማልማት ከሌሎች አካባቢዎችና መስህቦች ጋር በማስተሳሰር ትልቅ የቱሪስት መንደር እንዲሆን የተዘራውን ዘር መንከባከብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅን የተረከበው ኩሪፍቱ ሪዞርት አካባቢውን ትልቅ የቱሪስት መንደር ለማድረግ የበኩሉን ይጫወታል ብለዋል።
በዮናስ ጌትነት

