Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ..

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሪች ፎር ቼንጅ በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው አለ የትምህርት ሚኒስቴር ፡፡

ሪች ፎር ቼንጅ ኢትዮጵያ ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር የሚያከናውነው የ”ኢድቴክ ፌሎውሺፕ” ፕሮግራም የምክክርና የፈጠራ ውጤቶች ማሳያ መድረክ ተጀምሯል።

የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴዔታ ክንደያ ገ/ህይወት (ፕ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የትምህርት ጥራትን እና ተደራሽነትን ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት የአጋር አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው÷ የ”ኢድቴክ ፌሎውሺፕ” ፕሮግራም የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መርሐ ግብሩ ለትምህርት ዘርፉ ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ መንግሥት ዲጂታል ትምህርትን ለማጠናከር የሰጠውን ትኩረት የሚያጎለብት ነው ብለዋል፡፡

የሪች ፎር ቼንጅ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር መቅድም ጉልላት በበኩላቸው÷ ድርጅቱ በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ሥራ ፈጠራን ለማበረታታት በማሕበረሰቡ ወስጥ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን መፍታት የሚያስችሉ ሃሳቦች ያሏቸውን ሥራ ፈጣሪዎችን እያበረታታ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡

የዛሬው መርሐ ግብር በኢትዮጵያ ያለውን የትምህርት ሥነ ምህዳር በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን በማገዝ የተሻለ ተደራሽነት እና እመርታ ለማምጣት ያለመ ነው ብለዋል፡፡

በተጀመረው የአምስት ዓመት ፕሮግራም እስካሁን 24 የ”ኢድቴክ” ሥራ ፈጣሪዎችን ለእያንዳንዳቸው 60 ሺህ ደላር ከመስጠት ጀምሮ ሌሎች ድጋፎችን እያደረግን እንገኛለን ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም ሪች ፎር ቼንጅ የጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችን ክህሎት በማጠናከረ፣ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግና የገበያ ትስስር በመፍጠር ወደ ሥራ እንዲገቡ እያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በትምህርት ዘርፍ ላይ አዳዲስ የቴክኖሎጂ መፍትሄዎችን የፈጠሩ ወጣት ማህበራዊ ሥራ ፈጣሪዎችን አቅም ለመገንባት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ ቀርቧል፡፡

በዛሬው ሥነ ሥርዓት ላይ ወጣት የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪዎች የትምህርት ተደራሽነትን፣ ጥራትንና ፍትሃዊነትን የሚያረጋግጡ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለባለሀብቶችና ለፖሊሲ አውጪዎች ለዕይታ አቅርበዋል፡፡

ይህም የሀገሪቱን የትምህርት ሥርዓት ለማዘመንና የዲጂታል ትምህርት መሠረተ ልማትን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተመላክቷል፡፡

Exit mobile version