አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለሹዋሊድ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም የሹዋሊድ ምሽት ሐረር እንደ ጨረቃና ከዋክብት በሐረሪዎች ውብ ባህል፣ ልዩ ዜማና ትዕይንት የምትደምቅበት መሆኑን አውስተዋል፡፡
በዓሉ ከባህላዊ ሥነ ሥርዓትነቱ ባለፈ የጥንታዊቷ ጀጎል የታሪክ ዐሻራ፣ የሕዝቦች የአብሮነት መድረክና የኢትዮጵያ የባህል ብዝኃነት ማሳያ ነው ብለዋል።
ሹዋሊድ የማኅበራዊ ትሥሥር ድልድይ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ቂም በቀል የሚሻርበት፣ በወጣቱና በአረጋውያን መካከል ያለው የትውልድ ሠንሰለት በምርቃትና በምክር የሚታደስበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የአብሮነትና የመቻቻል ዕሴቶች በደመቀ ሁኔታ የሚታዩበት ልዩ ዓመታዊ ክብረ በዓል መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
መንግሥት ለሀገራዊ ቅርሶችና ለቱባ ባህላዊ እሴቶች ጥበቃ ልዩ ትኩረት የሰጠው እንደ ሹዋሊድ ያሉ ቅርሶችን የቱሪስት መስሕብና የሀገራዊ አንድነታችን ምሰሶ ሆነው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ነው ሲሉም አመልክተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ ጭምር ዕውቅናን ያገኘው ሹዋሊድ የሐረርን ብቻ ሳይሆን የሁላችንንም እንግዳ ተቀባይነትና የከበረ ዕሴት ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና አለው ነው ያሉት።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ለሐረሪ ሕዝብና ለከተማዋ ነዋሪዎች በሙሉ እንኳን ለሹዋሊድ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

