አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ ኮተቤ አካባቢ ያስገነባቸውን ሁለት የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ መሙያ ጣቢያዎችን አስመርቋል።
የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ዛሬ ከተመረቁት ሁለት የቻርጅ መሙያ ጣቢያዎች በተጨማሪ ሦስተኛው ጣቢያም በፒያሳ ተገንብቶ ተጠናቅቋል።
ተቋሙ በመጀመሪያው ምዕራፍ በአዲስ አበባ ከተማ 32 እንዲሁም በክልል ከተሞች 8 ጣቢያዎችን ለመገንባት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ የሀገር ገቢና ወጪ ንግድ በሚከናወንበት የጅቡቲ ኮሪደር ጣቢያዎችን የመገንባት እቅድ እንዳለው አመላክተዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በሪኦ ሀሰን በበኩላቸው÷ የጣቢያዎቹ መከፈት የአረንጓዴ ኢኮኖሚና ታዳሽ ኃይልን በመደገፍ የውጭ ምንዛሪን ለማስቀረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የኤሌክትሪክ መኪኖች መስፋፋትን ተከትሎ በዋናነት ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከል የቻርጅ ጣቢያዎች የሉም የሚለውን የሚመልስ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በ255 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነቡት እነዚህ 3 ጣቢያዎች በአጠቃላይ 30 የኤሌክትሪክ መኪናዎችን በአንድ ጊዜ ቻርጅ ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው።
እንደሀገር በ10 ዓመታት ውስጥ 2 ሺህ 300 የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎችን ለመገንባት መታቀዱም ተመላክቷል።
በእየሩሳሌም አበበ

