አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና ዘርፉ በፖሊሲ እንዲመራ መደረጉ በማዕድን ልማት ላይ ለታየው ፈጣን ለውጥ ትልቅ ሚና ተጫውቷል አሉ የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኝ (ኢ/ር)።
ሚኒስትሩ ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት÷ ዘርፉ ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ ተደርጎ በመወሰዱ ውጤታማ ስራ እንዲሰራ አስቻይ ሁኔታ ተፈጥሯል።
ባለፉት 8 ወራት በማዕድን ዘርፉ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸው÷ ይህንንም በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ወደ 5 ቢሊየን ዶላር ለማድረስ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የማዕድናት ዋጋ መጨመር፣ የምርት ጥራት ማስጠበቅ መቻል እና እሴት በመጨመር መመረቱ ለገቢው ዕድገት አስተዋጽዖ ማበርከቱን ጠቁመዋል።
የብሔራዊ ባንክ ለወርቅ ግዢ የሚያቀርበው ማራኪ የታሪፍ ዋጋና የተዘረጋው ህጋዊ የቁጥጥር ሰንሰለት ኮንትሮባንድን በመቀነስ ረገድ ትልቅ ኃይል ሆኗልም ነው ያሉት።
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካትና ወጪ ንግድን ለማሳደግ በተወሰደው ፈጣን ርምጃም ተጨባጭ ውጤቶች እየታዩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ቴክኖሎጂና መሰረታዊ መረጃዎችን በመጠቀም የሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን የማምረት አቅም በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ኩባንያዎች በሀገር ውስጥ እንዲሰማሩ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎች መፈጠሩን ጠቅሰው÷ በቀጣይም ማሕበረሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰፋፊ ስራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ በተወሰኑ ምርቶች ላይ ብቻ እንዳይወሰን የአቅርቦት ሰንሰለቱን የማሳደግ ሥራ በትኩረት ይከናወናል ሲሉም አስረድተዋል።
በቅድስት ዘውዱ

