Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በ7 ዓመታት ውስጥ የግብርና ምርት ወደ 150 ሚሊየን ቶን ከፍ ብሏል – የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ አጠቃላይ የግብርና ምርት በሰባት ዓመታት ውስጥ ከ41 ነጥብ 7 ሚሊየን ቶን ወደ 150 ሚሊየን ቶን ከፍ ብሏል አለ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት።
ጽ/ቤቱ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሽግግር ወደ ዘመናዊና ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚ በሚል ያለፉትን ስምንት የለውጥ ዓመታቱ ጉዞ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፥ የኢትዮጵያን የግብርና አብዮትና የምግብ ሉዓላዊነት ስኬቶች አስቀምጧል።
ኢትዮጵያ በስንዴ እርሻ ባስመዘገበችው እመርታ ሙሉ በሙሉ ራሷን መቻሏን የጠቆመው መግለጫው፥ በ2017 ዓ.ም በአፍሪካ ትልቋ የስንዴ አምራች ሀገር ለመሆን መብቃቷን አመላክቷል፡፡
በብዝሃ ሰብል ልማት አማራጭ አማካኝነት በተለይ የሩዝ፣ የቅባት እህሎችና ሌሎች ለኢንዱስትሪ ልማት የሚውሉ ሰብሎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውም ተገልጿል።
የእንስሳት ሀብትና ከፍተኛ ዕሴት ያላቸው የግብርና ምርቶች ፈጣን ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን፥ ዓመታዊ የእንቁላል ምርት 9 ነጥብ 4 ቢሊየን እንዲሁም የወተት ምርት 13 ቢሊየን ሊትር መድረሱን ጽ/ቤቱ ገልጿል፡፡
በተመሳሳይ የሥጋ ምርትም ወደ 10 እጥፍ በሚጠጋ መጠን ማደጉ በመግለጫው ተጠቅሷል።
በኩታ ገጠም እርሻ 9 ነጥብ 5 ሚሊየን አርሶ አደሮችን በ12 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ በማሳተፍ ተጨባጭ ውጤቶች የተገኘ ሲሆን፥ በዚህም የ29 በመቶ የምርታማነት ዕድገትና የ18 በመቶ የገቢ ጭማሪን የሚያካትት እንደሆነ ተጠቁሟል።
በአጠቃላይ የግብርና ምርት በሰባት ዓመታት ውስጥ ከ41 ነጥብ 7 ሚሊየን ቶን ወደ 150 ሚሊየን ቶን ከፍ ማለቱንና ከወጪ ንግድ ለሚገኘው ገቢ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን የጽ/ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡፡
በእነዚህ ዓመታት የቡና ምርት በአጥፍ አድጎ ወደ አንድ ሚሊየን ቶን የተጠጋ ምርት የተገኘ ሲሆን፥ በ2017 በጀት ዓመት ብቻ 2 ነጥብ 65 ቢሊየን ዶላር አስገኝቷል፡፡
Exit mobile version