Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከንቲባ አዳነች አቤቤ 6ኛውን የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ 6ኛውን አዲስ መሶብ ዲጂታል አንድ ማዕከል አገልግሎት በጉለሌ ክፍለ ከተማ ስራ አስጀምረዋል ።

ከንቲባዋ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው እንዳሉት፥ በሀገራዊ ለውጡ የመንግስት የተቋማት ስብራትን በመጠገን ነጻ፣ ገለልተኛ እና የአገልጋይነት መንፈስን የተላበሰ ጠንካራ ተቋማት በመገንባት ስኬታማ ሽግግር ተደርጓል፡፡

የአገልግሎት ዘርፉ ለዘመናት ስር በሰደደ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ተተብትቦ መቆየቱን ጠቅሰው፥ ችግሩን ሥር ነቀል በሆነ መልኩ ለመለወጥ የመሶብ ዲጂታል አንድ ማዕከል ለተገልጋዩ እፎይታን ይዞ መጥቷል ነው ያሉት።

መጋቢት 24 ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ የማሻገር ቃል ኪዳን የተገባበት ታሪካዊ ቀን ነው ያሉት ከንቲባዋ፥ ሀገራዊ ለውጡ ለሁሉም፣ ከሁሉምና በሁሉም የመጣ መሆኑን አውስተዋል።

ከለውጡ ወዲህ በጋራ ጥረት የሚታዩና ተጨባጭ የሆኑ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸው፥ ይህም የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ስብራቶቻችን እንዲጠገኑና ወደ ከፍታ እንድንጓዝ እጅግ ጠንካራ መሰረት የጣለ ነው ብለዋል።

እንሰራለን፥ እንችላለን ብለን በጋራ በተነሳንባቸው ዓመታት ከኋላ ቀር የፖለቲካ ባህሎች ተላቅቀን ችግሮችን በውይይትና በምክክር የመፍታት ሂደት ላይ ገብተናል ነው ያሉት።

ስምንት ዓመታት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሽግግር ወደ ዘመናዊና ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚ ለመገንባት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገብን እንገኛለን ሲሉም ገልጸዋል።

የተሰበሩ ማህበራዊ እሴቶችን በማከም ማህበራዊ ፍትህ እንዲነግስ የሚስችሉ በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን አስረድተዋል፡፡

በመዲናዋ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖችን በተለይም የሀገር ባለውለታዎችን፣ አቅመ ደካሞችን፣ አካል ጉዳተኞችንና ረዳት የሌላቸውን ወገኖች ከአስቸጋሪ ኑሮ አውጥተን የሰውን ክብር በሚመጥን መልኩ እንዲኖሩ አድርገናል ነው ያሉት።

ባዶ ምሳ ዕቃ ይዘው ወደ ትምህርት ገበታ ይመጡ የነበሩ ሕፃናትን እኩል በልተውና ለብሰው እንዲማሩ ከማድረግ ባለፈ አዲስ አበባን ሕፃናትን ለማሳደግ ተመራጭ ከተማ አድርገናታል ብለዋል።

የእነዚህ የለወጥ ፍሬዎች ዋነኛ ተጠቃሚ የሆነው የአዲስ አበባ ህዝብ ማልዶ ወደ አደባባዮች በመውጣት የዘወትር ድጋፉን አጽንቷል ያሉት ከንቲባዋ፥ መንግስት ከህዝቡ ጋር ያሳካው ድል እና የደረሰበት ርቀት ቀላል እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

Exit mobile version