Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ለራሷ የሚያስፈልጋትን መድኃኒት ማምረት አለባት – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ለራሷ የሚያስፈልጋትን መድኃኒት ማምረት አለባት የሚል እምነት በመያዝ እየሰራን ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የሳይንስ ሥነ ምሕዳር ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ዘመናዊ የምርምር ማዕከል በዛሬው ዕለት መርቀው ስራ አስጀምረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ በአንድ ሀገር ጉዞ ውስጥ መከራ፣ ችግርና ተግዳሮት አይፈጠር አይባልም ነገር ግን ይህ ሲፈጠር ያንን ወደ ዕድል ለመቀየርና ከችግሩ ውስጥ ዕድል ለማውጣት መስራት ለሰው ልጅ እንዲሁም ለሀገር በእጅጉ ያስፈልጋል ብለዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት የሰለጠነው ዓለም ያልሰለጠነውን ዓለም በተለይም አፍሪካን ሰው የሚያልቅበትና ከበሽታው የማይመልጥ አሕጉርና በየቦታው ሰው እየሞተ የሚታይበት ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች መገመታቸውንና መተንበያቸውን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ትንበያው ያልሰራ ቢሆንም ሂደቱ ዝግጅት ማድረግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን የሚያስተምር እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህም በምግብና በመድኃኒት ራስን ለመቻል እንደ ዕድል መጠቀም አለብን የሚል አቋም እንደ መንግሥት ወስደን ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ለዚያም በበጋ እንረስ መሬት በፆም አይደር በሚል ስንዴ ላይ በመዝመት ውጤት ያስመዘገብነው ብለዋል።

በተመሳሳይ በመድኃኒትም መሰል ርምጃ መወሰዱን ጠቅሰው÷ ኮሮና በተከሰተበት ወቅት ኢትዮጵያ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ማምረት የምትችለው መድኃኒት 8 በመቶ እንደሆነና የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ በመምጣት እንዲያመርት ቢጠየቅም ፍላጎት እንዳልነበረው አመልክተዋል።

መድኃኒት፣ ልብስ እንዲሁም ምግብ በበቂ አምርቶ የራሱን ፍጆታ የማይሸፍን ሀገር እንደሀገር ሉዓላዊ ሀገር ነኝ ብሎ መቀጠል እንደማይችል ጠቅሰዋል።

ምግብ፣ ልብስና መድኃኒት መሰረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን በመግለጽም በእነዚህ ሦስቱ ላይ ጠንክረን እንስራ የሚል ዕቅድ በመያዝ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በወቅቱ የነበረው 8 በመቶ የሀገር ውስጥ መድኃኒት አቅርቦት አሁን ላይ 40 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።

ይህም በቅርቡ የሚመረቁ ፋብሪካዎች በመኖራቸው በዚህ ዓመት መድኃኒት በሀገር ውስጥ የማምረት አቅም ከ50 እስከ 55 በመቶ እንደሚደርስ ጠቁመዋል።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም በመድኃኒት ኢትዮጵያ ለራሷ የሚያስፈልጋትን ማምረት አለባት የሚል እምነት በመያዝ እየሰራን ነው ብለዋል።

በአድማሱ አራጋው

Exit mobile version