አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ ሕልፈት የተሰማቸውን ኀዘን ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት የኀዘን መልዕክት÷ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው መስክ ያገለገሉት አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ በማረፋቸው የተሰማኝን ኀዘን ለመግለጽ እወዳለሁ ብለዋል።
አምባሳደር ቆንጂት ከልጅነት እስከ ዕውቀት ኢትዮጵያን በዲፕሎማትነት በማገልገል ከአምባሳደር ዮዲት እምሩ ቀጥለው ሁለተኛዋ ሴት የኢትዮጵያ አምባሳደር መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለሕግ፣ ለአሠራር፣ ለፕሮቶኮል እና ለኢትዮጵያ ጥቅሞች በነበራቸው የጸና አቋም እናስታውሳቸዋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ከእርሳቸው በኋላ አያሌ ሴት ዲፕሎማቶች በመስኩ እንዲሠማሩ መንገዱን አስፍተዋል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸው እና ለመላ ኢትዮጵያውያን መጽናናት ተመኝተዋል።

