Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሕዝባዊ ወገንተኝነት ያለውና ተልዕኮን በብቃት የሚወጣ የፖሊስ ኃይል ተገንብቷል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጸጥታ ዘርፍ ሪፎርም በሕግ ብቻ የሚሠራ፣ ሕዝባዊ ወገንተኝነት ያለውና ተልዕኮን በብቃት የሚወጣ የፖሊስ ኃይል ተገንብቷል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

20ኛው የፖሊስ ኮሚሽነሮች ጉባኤ “ፖሊሳዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የሀገርን ጥቅምና የሕዝብን ፍላጎት ያስከበረ የተልዕኮ አፈጻጸም መገንባት የሚያስችል የፖሊስ ዘርፍ ሪፎርም ተከናውኗል፡፡

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ትኩረት ከተሰጣቸው ሪፎርሞች አንዱ የፖሊስ ዘርፍ መሆኑን ገልጸው፥ በሪፎርሙ ብቁ የፖሊስ ባለሙያዎችን ለማፍራትና ጠንካራ ፖሊሳዊ ተቋም ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል ነው ያሉት፡፡

የመደመር መንግሥት የፖሊስ አገልግሎት ታማኝም አሳማኝም መሆን እንዳለበት ያምናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የፖሊስ አባላት ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝቡና ለኅሊናቸው ታማኝ ሊሆኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በሌላ በኩል የጸጥታ ኃይላችን የሚወስደው ሕጋዊ ርምጃ እንዲሁም የወንጀል መከላከልና ምርመራ ለሕዝቡ አሳማኝ በሆነ ሥርዓትና ሞራል መከናወን አለበት ብለዋል፡፡

ባለፉት ጊዜያት በባንዳና ባዳ ኃይሎች የተቃጡ ጥፋቶችን መከላከል በሪፎርሙ ከተገኙ አንኳር ውጤቶች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የጠላትን ተልዕኮ ተቀብለው የሚመጡ ሠርጎ ገቦችን በመከታተል፣ በማደንና ለሕግ በማቅረብ የፖለቲካና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ያለ ዕንቅፋት እንዲከናወኑ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ እና ነጻ ሆኖ እንዲካሄድ ሕዝቡ እና የጸጥታ ኃይሎች የተጣለባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት በብቃት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የምርጫው ሂደት ያለ እንቅፋት እንዲከናወን የጸጥታ ተቋማት እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በንሥር ዓይን መከታተልና የምርጫ ተሳታፊዎችን ደኅንነት በንቃት መጠበቅ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የምርጫውን ሂደት ለማደናቀፍ ከውጭና ከውስጥ የሚሠነዘረውን ጥቃት መከላከልና ለማምከን በትጋት መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በለይኩን ዓለም

Exit mobile version