Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሞጆ ደረቅ ወደብ መግቢያና መውጫ ኬላ የምግብና መድኃኒት ላቦራቶሪ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የጥራት ቁጥጥር ሥርዓትን ለማጠናከር የሚያስችል በሞጆ ደረቅ ወደብ መግቢያና መውጫ ኬላ የምግብና መድኃኒት ላቦራቶሪ አስጀምሯል።

የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ፍሬሕይወት አበበ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የተመረቀው የፍተሻ ሥርዓት የምግብና መድኃኒት ጤንነትን ለመቆጣጣጠር የሚረዳ በቴክኖሎጂ የታገዘ ላቦራቶሪ ነው።

የፍተሻ ሥርዓቱ የጥራት ቁጥጥር ሥርዓትን ለማዘመንና የሕዝብን ጤና ከማንኛውም አደጋ ለመጠበቅ የሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ወሳኝ ምዕራፍ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

በዓለም አቀፋዊ የንግድ እንቅስቃሴ ምርቶች በፍጥነት ከአንድ ሀገር ወደ ሌላው እንደሚሰራጩ ጠቁመው÷ሒደቱም ጥራታቸውን ያልጠበቁና ተመሳስለው የተሠሩ ምርቶች የሚዘዋወሩበትን ዕድል እንደሚያሰፋው አስረድተዋል፡፡

እነዚህን ምርቶች በመግቢያ ኬላዎች ላይ በመግታት የሚያደርሱትን ጉዳት መከላከል እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡

መሰል ምርቶች ታካሚው ከሕመሙ እንዳይድን ከማድረግ ባለፈ ለመድኃኒት መላመድና ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንዲሁም በአጠቃላይ በጤና ሥርዓቱ ላይ የሕዝብ እምነት እንዲሸረሸር እንደሚያደርጉ አብራርተዋል፡፡

መድኃኒቶችን ብቻ ሳይሆን የምግብ ምርቶችን ጨምሮ በድንበር ኬላዎች ላይ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ዛሬ የተጀመረው የሦስት ደረጃ የምርመራ ሥርዓት የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት ያግዛልም ነው ያሉት፡፡

የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በበኩላቸው÷ የማዕከሉን አገልግሎት አሳጣጥ ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡

የሥራ ቦታው ምቹ እንዲሆን እና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሞጆ ደረቅ ወደብ ያስጀመረው የፍተሻ ሥርዓት የአገልግሎት ቅልጥፍናን እንደሚጨምርም አስገንዝበዋል፡፡

በመቅደስ ከበደ

Exit mobile version