አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያና ጃፓን በወታደራዊ እና ፀጥታ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ተስማምተዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) በጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ አማካሪ ኦዌ ሳዳማሳ የተመራውን የልዑካን ቡድን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
በውይይታቸውም የሁለቱን ሀገራት ብሄራዊ ጥቅም፣ የጋራ ፍላጎትና እሴቶችን ባከበሩ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ በቅንጅት መስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ መክረዋል፡፡
አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) በዚህ ወቅት ጃፓን ለትብብር ያሳየችውን ተነሳሽነት በማድነቅ÷ ኢትዮጵያ በእውነተኛ ወዳጅነትና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ወታደራዊ አጋርነትን ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡
ይህ ትብብር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረውም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
ኦዩኢ ሳድማሳ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካም ሆነ በአህጉር ደረጃ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የምታከናውናቸውን ተግባራት አድንቀዋል።
በተለይም ሀገሪቱ በሰላም ማስከበር ረገድ ያላትን ሰፊ ተሞክሮ ከግምት ውስጥ በማስገባት ጃፓን በዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ጃፓን የኢትዮጵያን የሰላም ማስከበር ማዕከል አቅም ለመገንባት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን መናገራቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።
በስልጠና እና በልምድ ልውውጥ የመከላከያ ሠራዊቱን የሰው ኃይል የሙያ ብቃት ለማሳደግ ቁርጠኝነት መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡

