አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።
ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል እንኳን አደረሳችሁ
የትንሣኤ በዓል አራት ነገሮች የተሻሩበት ዕለት ነው። ሞት፣ መግነዝ፣ መቃብር እና ማኅተም።
ሞት እና መቃብር ከአዳም የመጡ ዕዳዎች ናቸው። ወደ አፈር ትመለሳለህ በመባሉ። መግነዝ የወዳጅ፣ ማኅተም የጠላት ናቸው።
ሰው በአራቱም ፈተና ይገጥመዋል። በተቀበለው ዕዳ፣ በዕዳው ምክንያት ከወዳጆቹ በሚያገኘው መግነዝ እና መነሣቱን የማይፈልጉት ጠላቶቹ በሚያትሙበት ማኅተም።
ወዳጆቹ ለምን ይገንዙታል? ማስነሣት ስለማይችሉ። ያላቸው አማራጭ ገንዘው ሞትን ያህል ዕዳ እንዲከፍል ማድረግ ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ የአዳምን የሞትና የመቃብር ዕዳ፤ የነዮሴፍን መግነዝ፣ የነ ቀያፋን የመቃብር በር ማኅተም ሽሮ – ትንሣኤውን ዐወጀ። ይህ ነው ትንሣኤን ታላቅ ዕለት፣ ታላቅ በዓል ያደረገው።
ኢትዮጵያውያን ሆይ። ያለፈ ዘመን ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዕዳ አለብን።
ይሄንን መሻር ሲያቅታቸው ወዳጆቻችን ያለበሱን የፖሊሲና የስትራቴጂ መግነዝም አለብን። ጠላቶቻችንም ከዕዳ እንዳንወጣ በር ዘግተውብናል። በሩ አልበቃ ብሏቸው ማኅተም አትመውበታል።
እኛን ግን የትንሣኤው ጌታ አስተምሮናል። ዕዳውን በሀገራዊ ምክክር፣ በሽግግር ፍትሕ እና በተሐድሶ ፕሮግራም እንሽራለን።
መግነዙን በሪፎርሞቻችን እንፈታለን። የተዘጋብንን በርም እንከፍታለን። ማኅተሙንም እናምክናለን።
የትንሣኤ ሌሊት – ሌሊት ናት ተብላ ነበር። በእኩለ ሌሊት ግን የትንሣኤ ብርሃን አጥለቀለቃት። ለተኙት ሌሊት፣ ለነቁት ብርሃን ሆነ።
ሌሊታችን የመጣ ለመሰላቸው ሁሉ፤ ለእኛ ግን ትንሣኤያችን መሆኑን እናውጃለን። ትንሣኤያችን ግን ለነቁ እንጂ ለተኙ አይታይም።
የተኙትማ እስኪነጋ ድረስ ክርስቶስ መነሣቱን አያውቁም ነበር!
በድጋሚ መልካም በዓል ይሁን።

