አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር በመሆን የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ አጋርተዋል፡፡
በመላው ኢትዮጵያ በክርስትና ጥላ ውስጥ በሚገኙ ቤተ-እምነቶች ያሉ ክርስቲያኖች የትንሳኤን በዓል በተስፋ፣ በመስዋዕትነት እና በአዲስ መነሳት መንፈስ በአንድነት ያከብራሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ዓመታዊውን የፋሲካ ማዕድ ማጋራት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በአንድነት ፓርክ በጋራ መታደማቸው ለእውነተኛው የአንድነት መንፈስ ጉልህ ማሳያ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል።
ከሳምንታት የፆም፣ ጥሞና እና ራስን የመመልከት ጊዜ በኋላ ፋሲካ በእውነተኛ አምልኮ፣ መንፈስን አድሶ፣ ቤቶችንም በደስታ ይሞላል፣ በዘመድ አዝማድ መጠያየቅ እና ማዕድ መካፈልም ፍቅርን እንደሚያዳብር ተገልጿል።
በዓለ ትንሳኤው በመላው ኢትዮጵያ የእምነት፣ ቤተሰባዊነት እና የመታደስ መንፈስ የሚታይበት መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ሁላችንም በዚህ የትንሳኤ መንፈስ ዛሬም፣ ነገም፣ ሰርክ ቤታችንን፣ ልባችንንም ለተቸገሩ ወገኖች መክፈት አለብን ብሏል፡፡

