አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች ለመላው አፍሪካ ኩራት ናቸው አሉ የላይቤሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳራ ቤይሶሎው ኒያቲ።
በሚኒስትሯ ሳራ ቤይሶሎው ኒያቲ የተመራ ልዑክ የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክን ጎብኝቷል።
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ዘርፍ የታዩ ለውጦች ለመላው አፍሪካ ኩራት ናቸው።
ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያላቸውን ፍላጎት ገልጸው÷ በተለይም በቴክኖሎጂ፣ ግብርናና ትምህርት ዘርፎች ላይ በትብብር በመስራት የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል።
አፍሪካ ያላትን ሰፊ የሰው ኃይል በተለይም ወጣቶችን በአግባቡ ለመጠቀም በ”ደቡብ-ደቡብ” ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአፍሪካ ደረጃ በጋራና በቅንጅት ከተሰራ አህጉሪቷን በልማት ማሳደግ እንደሚቻልም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአይ ሲቲ ፓርክ የተመለከቷቸውን የዳታ ማዕከላት ኢትዮጵያ በውጭ አገልግሎት አሰጣጥ እና በፈጠራ ረገድ በአህጉሪቱ ተወዳዳሪና የማይበገር አቅም እየገነባች መምጣቷን ያሳያል ብለዋል።
በተለይም ወጣቶች አዳዲስ ግኝቶችን እንዲያመነጩ በፓርኩ ውስጥ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ እንደሚሆንም አመልክተዋል።
የዳታ ማዕከሉ አፍሪካ የራሷን መረጃ በራሷ አቅም የመያዝ ብቃት እንዳላት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው÷ ላይቤሪያ ከኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ተሞክሮ በመቀመር የራሷን የዳታ ማከማቻ ማዕከል ለመገንባት ያላትን ፍላጎት አረጋግጠዋል።
ጉብኝቱ በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ተግባራዊ የኢኮኖሚ እና የቴክኖሎጂ አጋርነት የሚያሸጋግር መሆኑን የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል።
በላይቤሪያው ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ንዩማ ቦአካይ የተመራ ልዑክ ለስራ ጉብኝት ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል።

