አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሁን ባለንበት ዘመን ኢንዱስትሪ ከጭስና ብረት በተጨማሪ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን አካትቷል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የሉዓላዊነት ልብ” በሚል መሪ ሐሳብ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ስለ አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸው ኢንዱስትሪ 4.0 (አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት) በተለምዶ ከሚታወቀው የጭስ እና ብረት የኢንዱስትሪ እሳቤ ባሻገር ‘ቺፕስ እና ዳታን’ ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል።
ቺፕስ እና ዳታን ያላካተተ ኢንዱስትሪ የተሟላ ኢንዱስትሪ አይደለም የሚል እሳቤ መኖሩን ጠቅሰው፤ በ4.0 ውስጥ የሚጠቀሰው አንዱ አንጓ ጉዳይ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ነው ብለዋል።
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ከዚህ ቀደም በሩቅ እንደምናስበው ሳይሆን አሁን በየጓዳችን ገብቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዓለም ሀገራት የአየር ትራንስፖርት እንቅስቃሴን በቀላሉ ማወቅና መረጃን ማግኘት ያስችላል ነው ያሉት፡፡
አሁን ባለው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርንት እንኳን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በከፍተኛ ሁኔታ በጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል ብለዋል፡፡
በብዙ ተቋማት ውስጥ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ድምጽ አልባ የቦርድ አባል በመሆን ይሰራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲም ያለድምጽ የሚሳተፍ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የቦርድ አባል እንዳለ ጠቅሰዋል።
በዚህም ምንም እንኳን ድምጽ ባይሰጥም የቦርዱ አባላት በሚከራከሩባቸው ጉዳዮች አስተያየት ይሰጣል ነው ያሉት፡፡
የቦርድ አባላቱም ከዚህ በመነሳት ውሳኔ እንደሚያሳልፉ ነው ያነሱት።
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በኢንዱስትሪ ውስጥ እያመጣ ያለው ለውጥ አስገራሚ መሆኑን በማንሳት ገበያን ለማስተሳሰር፣ ለፍጥነት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
በሁሉም የሰው ልጆች የኑሮ እንቅስቃሴ ውስጥ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሮቦቶችም ፋብሪካን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ሰውን በመተካት እየሰሩ መሆናቸው የኢንዱስትሪው እድገት የደረሰበትን ደረጃ የሳያል ነው ያሉት፡፡
ከላይ በተጠቀሱት ሁኔታዎች ከዚህ ቀደም የነበረው የኢንዱስትሪ እሳቤ በብዙ መቀየሩን እና የጥራት ደረጃው መጨመሩን አንስተዋል፡፡
በአቤል ነዋይ

