አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከብዛት ይልቅ ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲገነቡ ተደርጓል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የሉዓላዊነት ልብ” በሚል መሪ ሐሳብ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለኢኮኖሚ እድገት አስፈላጊ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከተበተኑ ፋብሪካዎች በተሻለ ሁኔታ ኢንቨስትመንትን የሚሰቡ፣ የመሰረተ ልማት ወጪን የሚቀንሱ፣ የተቀናጀ አገልግሎት ለመስጠት እና ለአስተዳደር የሚመቹ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ለወጪ እና ገቢ ንግድ ምቹ እንዳልነበረ አስታውሰው÷ ፓርኮቹ በቂ ጥናት ያልተደረገባቸውና ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ የሚሰሩ ነበሩ ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከብዛት ይልቅ ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲገነቡ ተደርጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በዚህም የግንባታ ወጪን የሚቀንሱ እና የኢኮኖሚ እድገቱን የሚያሳልጡ ተደርገው መገንባታቸውን ነው ያስገነዘቡት፡፡
በተለይም ከለውጡ በኋላ ስራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በፓርኮቹ ግንባታ ከመንግሥት በተጨማሪ የግሉ ዘርፍ እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸው÷ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 26 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ሰባቱ የግል መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ

