Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ፍላጎታችን ኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ማድረግ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፍላጎታችን ኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ማድረግ ነው አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የሉዓላዊነት ልብ” በሚል መሪ ሐሳብ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የሚያሳድግ ሰፊ ስራ መሰራቱን አብራርተዋል።

ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ባሻገር ለማኑፋክቸሪንግ ማዕከልነት ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮች ላይ መሰራቱን ገልጸው÷ ሎጂስቲክስ፣ ንጹህና ታዳሽ ኃይል እንዲሁም ዲሞግራፊ ላይ መሰራቱን ተናግረዋል።

ሎጂስቲክስ ላይ አሁንም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው÷ በአብነትም የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክትን ጠቅሰዋል።

የሚገነባው አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ትልቁና የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ማዕከል ነው ብለዋል።

ኢንቨስትመንቱ ቀላል ባይሆንም በብዙ መልኩ ዕድል ስላለን ግንባታው በአየር ላይ ያለውን ትራንስፖርት በአፍሪካ ውስጥ ጎልቶ እንዲቀጥል ያስችላል ነው ያሉት።

ከአየር መንገዱ በተጨማሪ ፕሮጀክቱ ብዙ ነገር እንደሚስብ አንስተዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ በኮይሻ፣ በሶላር፣ በኑክሌር የተጀመረውን ጨምሮ ንጹህና ታዳሽ ኃይል ላይ ማምረት ለውድድር በእጅጉ አዋጭ ነው ብለዋል።

በዲሞግራፊ ረገድ ኢትዮጵያ ወጣት ያለባት ሀገር መሆኗን ገልጸው÷ ወጣቶች ላይ ከታች ጀምሮ ስለምንሰራ ተምረው ከተዘጋጁ ለክህሎት ምላሽ ይሰጣሉ ሲሉ ገልጸዋል።

አብዛኛው ወጣት ለቴክኖሎጂ የሚሳብ በመሆኑ በ5 ሚሊየን ኮደርስ በሰራነው ስራ አብዛኛው ሰው ከኮዲንግና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር እንዲተዋወቅ እያደረግን ነው ብለዋል።

በዚህ ምክንያት ቴክኖሎጂ የሚገነዘቡ የተማሩ ወጣቶች እየተፈጠሩ ሲሄዱ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለመሆን ዕድል ይፈጥራል በማለት አብራርተዋል።

ፖሊሲያችን ገበያው ላይ የግል ዘርፉን የሚያግዝ እንዲሆን ተደርጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ቦንድ ብለን ሀብት የምናስርበት መንገድ መቅረቱና አብዛኛውን ብድር ወደ መንግስት ማድረጋችን መቅረቱ የግል ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ እንዲነቃቃ አድርጓል ብለዋል።

ትኩረታችን ስትራተጂክ ምርቶች ላይ ነው፤ ሶላር፣ ፋርማሲቲካል፣ ኬሚካል፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እንዲሁም ኤሮስፔስ የትኩረት አቅጣጫ ስለመሆናቸው አንስተዋል።

እነዚህ ምርቶች ላይ መስራት በእጅጉ አዋጭ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአቢይ ጌታሁን

Exit mobile version