Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በጤናው ዘርፍ ጥቅም ላይ ለማዋል …

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰው ሰራሽ አስተውሎት በጤናው ዘርፍ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማስቻል እየተሰራ ይገኛል፡፡

ጤና ሚኒስቴር ከላስት ማይል ሄልዝ ጋር በመተባበር ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ድጋፍ የሚሰጥ ‘ኤችኢፒ አሲስት’ የተሰኘ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚሰራ አዲስ ቴክኖሎጂ የትግበራ ምዕራፍ የማስተዋወቂያ መድረክ እያካሄደ ነው፡፡

በጤና ሚኒስቴር የመጀመሪያ የማሕበረሰብ አቀፍ ተሳትፎ መሪ ሥራ አስፈጻሚ እስራኤል አታሮ በመድረኩ እንዳሉት፤ የጤናውን ዘርፍ ለማዘመን በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምን ማዕከል ያደረገ የማዘመን ስራ ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

የትግበራ ምዕራፍ ላይ የምትገኘው ‘ሀዋ’ የተሰኘችው የሰው ሰራሽ አስተውሎት የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችን ስራ በመደገፍ ረገድ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ታስችላለች ብለዋል።

ባለሙያዎች አስቸጋሪ የሕክምና ጉዳዮች ሲያጋጥሟቸው ‘ሀዋ’ በተሰኘች የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ እገዛ የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ጠቁመዋል።

ቴክኖሎጂው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች መደበኛ ሥራቸው ላይ የተሻለ እገዛ በማድረግ ውጤታማ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል ነው ያሉት፡፡

የላስት ማይል ሄልዝ ቺፍ ቴክኒካል ኦፊሰር ዲቪያ ናይራ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ የመሪነት ሚናን እየተጫወተች ትገኛለች ብለዋል።

ቴክኖሎጂው የጤና ሚኒስቴር ካዘጋጃቸው 100 የተረጋገጡ የሕክምና መመሪያዎች ላይ ብቻ በመነሳት እገዛ የሚያደርግ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version