አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኦሮሚያ ክልል የገበታ ለትውልድ መርሐ ግብር አካል የሆነውን የሀሮ ደንዲ ሎጅን በዛሬው ዕለት መርቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትርሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ ይህ ስፍራ የተፈጥሮን ሥነ ምህዳር የጠበቀ የቱሪዝም መዳረሻ ከመሆኑ ባለፈ ዘመናዊ ሥነ ሕንጻ ከተፈጥሮ የልብ ትርታ ጋር የተዋሃደበት የኢትዮጵያ አዲስ ገጽታ ነው ብለዋል።
በዚህ ቦታ የቆመው ግንባታ ብቻ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ይልቁንም የተፈጥሮ ቅርሳችንን በማክበር የደንዲ ክሬተር ሐይቅን ነባራዊ ውበት ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተርፍ መደረጉን አመልክተዋል፡፡
ይህም የአካባቢውን ማህበረሰብ ባህላዊ እሴት ባከበረ እና ሰው ተኮር በሆነ መልኩ መሬቱን ለመንከባከብና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተገነባ ስፍራ ነው ብለዋል።
የሀሮ ደንዲ ሎጅ የገባነውን ቃል ፈጽመን የመገኘታችን ተጨማሪ ማረጋገጫ ነው ሲሉም አስረድተዋል።
ሎጂው እና የአካባቢው አስደናቂ ሥነ ምህዳር ኢትዮጵያን ለመጎብኘት፣ ለኢንቨስትመንት እና ለሁነት ቱሪዝም ተመራጭ መዳረሻ እንደሚያደርጋት አብራርተዋል፡፡
ቱሪዝም የኢኮኖሚያችን አንዱ ምሰሶ እንደመሆኑ የሀገራዊ ዕድገታችንን የወደፊት አቅጣጫ እየቀረጸ ያለ ዘርፍ መሆኑን እያስመሰከረ ነው ብለዋል፡፡

