አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀየስነው አዲሱ የኢኮኖሚ አካሄድ በአጭር ጊዜ ትግበራ ጠንካራ ባለሁለት አሃዝ የእድገት ሂደትን አስመዝግቧል አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባወጡት መረጃ፤ ዛሬ ጠዋት የስራ ዘመኑን ሶስተኛ የ100 ቀናት የመንግሥት ሥራ አፈፃፀም ከዘጠኝ ወራት አጠቃላይ አፈፃፀም ጎን ለጎን መገምገም ጀምረናል ብለዋል።
ለእድገት አመቺ ካልነበረ እና በደካማ የተቋማት እና የፖለቲካ ማዕቀፍ፣ በታጠረ የግል ዘርፍ ተሳትፎ እንዲሁም ውጤታማ ባልነበረ የቁጥጥር ከባቢ ከሚገለጠው የኢኮኖሚ መልክ መውጣት መቻሉን ገልጸዋል።
የግሉ ዘርፍ ደካማ ውድድር ውስጥ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመንግሥት ሥር የነበሩ በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው የንግድ ተቋማትም ከፍ ባለ የዕዳ ሸክም ተዘፍቀው ከአቅም በታች ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ይታወቃል ሲሉ ተናግረዋል።
ምርታማነት አሽቆልቁሎ ኢኮኖሚውም ለአየር ንብረት ለውጥ በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ ምላሽ በሚሰጥ አዲስ ገቢር ነበብ የፖለቲካ ኢኮኖሚ መንገድ ቀይሰናል ብለዋል።
የቀየስነው አዲሱ የኢኮኖሚ አካሄድ በአጭር ጊዜ ትግበራ ጠንካራ ባለሁለት አሃዝ የእድገት ሂደትን አስመዝግቧል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት ኢኮኖሚው በ9 ነጥብ 2 በመቶ እያደገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ እድገቱ በመጪው ዓመት ወደ10 ነጥብ 2 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
በየዘርፉም የታቀዱ ግቦቻችንን ለማሳካት ከፍ ባለ ትጋት ቀጥለን፤ በግብርና 7 ነጥብ 9 በመቶ፣ በኢንዱስትሪ 13 ነጥብ 2 በመቶ፣ በአገልግሎት 9 ነጥብ 3 በመቶ ዕድገቶች ሳይቆራረጡ የሚከናወኑ ይሆናል ብለዋል።
ይህ ጥረት የበለጠ ጽኑ፣ ተወዳዳሪ እና አካታች ኢኮኖሚ ለመገንባት ያለንን አቋም እና የመተግበር ዐቅም ያሳያሉ ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

