Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ስብስባ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 54ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች እንደሚከተለው ቀርቧል።

1. በቅድሚያ ምክር ቤቱ የተወያየው በሁለት የፋይናንስ ድጋፍና ብድር ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያው ለአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ ማስፈጸሚያ የሚውል ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ የሰማንያ ሚሊዮን (80,000,000) ዩሮ ብድር ስምምነት ነው፡፡

ሁለተኛው ለአነስተኛ የገጠር ገንዘብ አቅርቦት ማሻሻያ ፕሮግራም የሚውል ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የአንድ መቶ አስር ሚሊዮን (110,000,000) ዩሮ ብድር ስምምነት ነው፡፡

ምክር ቤቱ ሁለቱም የብድር ስምምነቶች ከአገራችን የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ የብድር ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው በሀገራችን የዩሪያ ማዳበሪያ ማምረቻና ማቀነባበሪያ ፋብሪካን የሚመለከት የኢንቨስትመንት ማበረታቻና ጥበቃ ስምምነት ላይ ነው፡፡

የስምምነቱ ዋንኛ ግብ አበዳሪዎች እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገራት ውስጥ ለሚሰሩ ፕሮጀክቶች ብድር ለመስጠት የሚጠቀሟቸውን ጠንካራ መስፈርቶች በማሟላት የሚያስፈልገውን ካፒታል እንዲያገኝ አስቻይ ሁኔታን መፍጠር፣ ማዳበሪያን በሀገር ውስጥ በማምረት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ማሟላት፣ ለማዳበሪያ ግዥ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት እና በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል የምናደርገውን ጥረት ማሳካት ነው፡፡

ምክር ቤቱም ስምምነቱ የመንግስትን የፖሊሲ አቅጣጫ የተከተለ መሆኑን በማረጋገጥ የገንዘብ ሚኒስቴር እንዲፈራረምና ወደ ስራ እንዲገባ በሙሉ ድምጽ ይሁንታ ሰጥቷል፡፡

3. ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው የቁልፍ መሠረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን መሠረት የሚያደርጉ የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶች በሚይዟቸው ኢንፎርሜሽኖች እና ዳታዎች ላይ የሚነጣጠሩ የሳይበር ጥቃቶች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ሰላምና መረጋጋት ላይ የሚፈጥሩትን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስና ለመከላከል ስጋትን መሠረት ያደረገ የቁልፍ መሠረተ ልማቶች ልየታ በማድረግ የሳይበር ደህንነት ጥበቃና ቁጥጥር ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

4. እንዲሁም ምክር ቤቱ በ6 አለም አቀፍ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ላይ ተወያይቷል፡፡

የመጀመሪያው ከቬትናም ሶሻሊስት ሪፐብሊክ መንግሥት እና ከሩሲያ ፌዴሬሽን ጋር የተደረጉ እንደ ቅደም ተከተላቸው የዲፕሎማቲክ ወይም የአገልግሎት ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን የማስቀረት ስምምነት እና የጋራ የባዮሎጂ ምርምር ማዕከል ማቋቋም ስምምነት ናቸው፡፡

ስምምነቶቹ ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እና በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ዘርፍ የምታደርገውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ እንዲያስችሉ ለምክር ቤቱ ቀርበዋል፡፡

ሁለተኛው ከኢስዋቲኒ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት፣ ከአንጎላ ሪፐብሊክ መንግሥት፣ ከባንግላዴሽ ሕዝባዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና ከሴራሊዮን ሪፐብሊክ መንግሥት ጋር በተደረጉ አራት የአየር አገልግሎት ስምምነቶች ላይ ተወያይቷል፡፡

ስምምነቶች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሀገራቱ ርዕሰ መዲናዎች በ3ኛ እና 4ኛ የትራፊክ መብት የመንገደኛና የጭነት የበረራ ምልልስ ለማድረግ፣ ተወካይ አየር መንገዶችን በሽርክና ለማሰራት፣ በ5ኛ የትራፊክ መብት ወደ ተመረጡ መዳረሻዎች በረራ ለማድረግ የሚያስችሉ እና ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር፣ ለአየር መንገዱ ተጨማሪ የገበያ ዕድል ለመፍጠር፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለማበረታት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት እና ለቱሪዝም ትልቅ ጠቀሜታ ያላቸው በመሆኑ ለምክር ቤቱ ቀርበዋል፡፡

ምክር ቤቱም በጉዳዮቹ ላይ ከተወያየ በኋላ የስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆቹ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

5. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ እሳት እና ሌሎች ቅጽበታዊ አደጋዎች አገልግሎት ማቋቋሚያ ደንብ ላይ ነው፡፡ አገልግሎቱ የእሳት እና ሌሎች ቅጽበታዊ አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠር የሚያጋጥሙ አደጋዎች የከፋ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ሳያስከትሉ ለመቆጣጠር፣ የልማትና የኢንቨስትመንት ተግባራት የእሳትና ሌሎች ቅጽበታዊ አደጋዎች ተጋላጭነትን በመፈተሽ ስጋት ካለ የምላሽ አቅም ግንባታ የምክር አገልግሎት ከሌለም ይሁንታ ለመስጠት እና ሀገራዊ የእሳትና ሌሎች ቅፅበታዊ የአደጋ ስጋትና ክስተት ቁጥጥር ስርዓትን ለመምራት እንዲችል ደንቡ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
#PMOEthiopia

Exit mobile version